በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ከበደ ገመቹ ዛሬ ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቧል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረውና ሸሽቶ በነበረበት አዳአ ድሬ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሃምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋለው ከበደ ገመቹ ዛሬ ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አረዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ በተጠርጣሪው ላይ በርካታ የምርመራ ስራ ማከናወኑን ለችሎቱ አስረድቷል።
በተጠርጣሪ እጅ ላይ የተገኘው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ መመርመሩን ገልጿል።
በተጠርጣሪው ላይ የተደረገ የቴክኒክ ምርመራ ውጤት መምጣቱን ተከትሎ ይህን ሰፊ ትንተና ውጤት ለመተንተን ጊዜ እንደሚያስፈልገው ለችሎቱ ገልጿል።
ተጠርጣሪው ከበደ ገመቹ በበኩሉ በአስተርጓሚ በኩል በሰጠው አስተያየት ከተያዘ ከአንድ ወር ከ16 ቀን በላይ እንደሆነው ጠቅሶ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የተገደለበት ሽጉጥ የኔ አይደለም ሲል ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲፈቅድለት ጠይቋል።
መርማሪ ፖሊስም ሽጉጡ የተጠርጣሪው መሆኑን ለችሎቱ አብራርቷል፤ በግድያው ወቅት በቦታው እንደነበር ጠቅሷል።
ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱ ለፖሊስ የምርመራ ውጤት ትንተና ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገዋል ሲል የ10 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል።
በሌላ በኩል አርቲስት ታረቀኝ ሙሉ በህገወጥ የሰዎች ዝወውር ወንጀል በተከሰሰ ጓደኛው ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮችን በገንዘብ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ ወንጀል ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
መርማሪ ፖሊስ በተጠረጠረበት ወንጀል ስድስት የሰው ምስክር ቃል መቀበሉን፣ የተሽከርካሪና የመኖሪያ ቤቱ ብርበራ መደረጉን፣ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል መቀበሉን፣ አሻራ ማስነሳቱን እና የተጠርጣሪ ስልክ መልዕክቶችን ለማስመርመር ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት መላኩን ለችሎቱ አብራርቷል።
በተጨማሪም ከዱባይ በሃዋላ የተላከ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለምስክሮች ምስክር ማባባያ የሚከፈል ክፍያ በባንክ ገብቶ መገኘቱን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፥ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ መጠቀም ወንጀል ምርመራ እየተደረገ መሆኑን እና ከባንክ የምርመራ ውጤት እየጠበቀ መሆኑንም ተናግሯል።
ተጠርጣሪው ኪዳኔ ዘካሪያስ የተባለ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ከተከሰሰ ግለሰብ ጋር ጓደኛ መሆኑን የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ ዱባይና በሃገር ውስጥ አብረው እንደሚሰሩ ጠቅሷል።
በተጨማሪም የኪዳኔ ዘካሪያስ ወንድም ወደ ሊቢያ ከሚሄዱ ሰዎች ብር እየተቀበለ በመኒ ላውንደሪ እንደሚመነዝር እና በጋራ እንደሚሰሩም አስረድቷል።
ተጠርጣሪው እነዚህ በገንዘብ ምስክርነት ቃላቸውን እንዲቀይሩ እያባበሏቸው የሚገኙ ምስክሮችን ከኪዳኔ ጠበቃ ጋር የማገናኘት ስራ መሰራቱን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል ለችሎቱ።
ለተጨማሪ ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩሉ ታረቀኝ ከኪዳኔ ዘካሪያስ ጋር መከሰስ የለበትም፣ በሙያው የሚተዳደር አርቲስት ነው፣ መርማሪው ያቀረበው የህግ መሰረት የለውም፣ ፍርድ ቤቱን የሚያሳምን ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል የሚሉ መቃወሚያዎችን አንስቷል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተጨማሪ ምርምራ የሰባት ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ