የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ አቅጣጫ ተቀመጠ

By Tibebu Kebede

August 26, 2020

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ በሚገኙ የልማት ፕሮጀክት ግንባታዎች ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ከኮንስትራክሽን ቢሮ፣ ከመንገድ ባለስልጣን እንዲሁም ከሜጋ ፕሮጀክት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እና ልማትን ለማፋጠን ይቻል ዘንድ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው በግንባታ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በውይይቱ ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ዕቅድ መሰረት እየሄዱ እንደሚገኙ ማወቃቸውን ምክትል ከንቲባዋ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

ነገር ግን ከአሁን በፊት ከነበረው የሥራ ሰዓት የተሻለ ርብርብ ማድረግ  እንደሚገባም ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም በውይይቱ ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮች ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት አልቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ የተጀመሩ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የግንባታ ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንሚያደርግ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡