Fana: At a Speed of Life!

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከ700 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከ700 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ 14ኛ የፌዴራልና የክልሎች ኢንቨስትመንት መስሪያ ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ በሀረር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የምክክር መድረኩ “ሰላም ለኢንቨስትመንትና ዜጎች ተጠቃሚነት የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ሰላማችንን እንጠብቅ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

በዓመታዊ የምክክር መድረኩ ላይ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከ700 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን በኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዕቅድ ዝግጅትና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ንዋይ ተድላ ገልፀዋል።

በሩብ ዓመቱ ከዘጠኝ የመንግስትና የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርተው ወደ ወጪ ከተላኩ የኢንደስትሪ ምርቶች ከ47 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱ ነው የተገለጸው።

ይህም የእቅዱን 71 በመቶ እንደሚሸፍን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም አዳዲስ ባለሃብቶች ምርቶቻቸውን ወደ ወጪ መላክ በመጀመራቸው የ88 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃም በዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ከ2 ሺህ 700 በላይ ባለሃብቶች የኢንቨስትመት ፍቃድ ተሰጥቷል ነው ያሉት።

በምክክር መድረኩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ የክልልና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት አለመረጋጋቶች በኢንቨስትመንቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም ከኤሌክትሪክ ኃይልና ከውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ ባለሃብቶች ችግር እየገጠማቸው መሆኑን አንስተዋል።

ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ኢንቨስት ለማድረግ ፍቃድ የወሰዱ ከ295 በላይ ባለሃብቶች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት እስከ 3 ሚሊየን ብር ከፍለው አገልግሎቱን ማግኘት ባለመቻላቸው በመማረር ስራው እስከመተው መድረሳቸውን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያት ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መ/ኮሚሽነር አቶ አንተንህ አለሙ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት አለመረጋጋቶች በኢቨስትመንት ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን አስታውሰዋል።

በተለይም ከባለድርሻ አካላት ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ለማስተካከል በፖሊሲና ስትራቴጂ የተደገፉ ምላሾችን ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ልማታዊ የሆኑ ባለሃብቶን ልየታና መረጣ ላይ ለኢንቨስትመንት ምቹና እምቅ አቅም ያላቸውን አካባቢዎች ጠቋሚ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑንና ቀልጣፋ አሰራርን ለመተግበር የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየተተገበረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሀረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አብዱልሃኪም አብዱማሊክ፥ በክልል ተከስተው የነበሩ አለመነረጋጋቶች በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸውን አስረድተዋል።

መድረኩ በችግር ውስጥ አልፈው ውጤታማ አፈፃፀም ካስመዘገቡ ክልሎች ልምድና ተሞክሮ በመቅሰም ወደ ተግባር በመቀየር የተሻለ ለመፈፀም እንደሚጠቅማቸው አንስተዋል።

በውይይት መድረኩ የ2012 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፥ የቀጣይ አስር ዓመታት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ረቂቅ እቅድ ቀርቦ ምክክር እንደሚካሄድበት ለማወቅ ተችሏል።

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.