Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ ከነባሩ አዋጅ ጋር ሲነፃፀር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲስ በቅንጦት እቃዎች ላይ (ኤክሳይዝ ታክስ) የሚጣለው ቀረጥ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወቃል።

ረቂቅ አዋጁ መንግስት ተገቢውን ግብር መሰብሰብ እንዲችል የሚያግዝ፣ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ አስተዋፅኦ የሚያደርግ እንዲሁም የህብረተሰቡን ጤና በሚጎዱ እና የማህበራዊ ችግር በሚያስከትሉ በተጨማሪም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ እቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ቀረጥ መጣል በማስፈለጉ መዘጋጀቱም ተገልጿል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል።

ለመሆኑ አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ከነባሩ አዋጅ ጋር ሲነፃፀር ምን ልዩነቶች አሉት?

ተሽከርካሪዎች

ከ1 ሺ 300 ሲ ሲ የማይበልጡ ተሽከርካሪዎች

በስራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በሁሉም የምርት ዘመን የሚገኙ ማለትም አዲስም ሆኑ አሮጌ፥ የሲሊንደር መጠናቸው ከ1 ሺ 300 የማይበልጡ ተሽከርካሪዎች የ30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጥላል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲገጣጠሙ ተበትነው የሚገቡ፣ በከፊል ተበትነው የሚገቡና አዲስ ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው የቀረቡም በተመሳሳይ 30 በመቶ እንዲሁም

እስከ 2 ዓመት ያገለገሉ – 80 በመቶ

እስከ 4 ዓመት ያገለገሉ – 130 በመቶ

እስከ 7 ዓመት ያገለገሉ – 230 በመቶ

ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ ከሆኑ ደግሞ 430 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጥላል።

እስከ 1 ሺህ 800 ሲ ሲ በሚሆኑት ላይ ደግሞ ነባሩ አዋጅ በሁሉም የምርት ዘመን 60 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል ይደነግጋል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መሰረት ደግሞ

አዳዲስ የሚገጣጠሙና በከፊል ተበትነው የቀረቡ እንዲሁም አዲስ ተገጣጥመው የገቡ ከሆኑ 60 በመቶ

እስከ 2 ዓመት ያገለገሉ- 110 በመቶ

እስከ 4 ዓመት ያገለገሉ- 160 በመቶ

እስከ 7 ዓመት ያገለገሉ- 260 በመቶ

ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ ከሆኑ ደግሞ – 460 በመቶ ኤክሳይዝ ታክሰ ይጣልባቸዋል።

ከ1 ሺ 800 ሲ ሲ በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ነባሩ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በሁሉም የምርት ዘመን ለሚገኙ የ100 ፐርሰንት እንዲቀረጡ ያዛል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ከአዲስ እስከ 7 አመት እና ከዛ በላይ የአገልግሎት ጊዜያቸው ከ30 እስከ 500 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጥላል።

በትምባሆ ምርቶች ላይ በስራ ላይ ባለው አዋጅ የነበረው 20 በመቶ ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከ20 እስከ 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጥል ይሆናል።

ጨው እንዲሁም ስኳርና ከስኳር የተገኙ ጣፋጭ ምርቶች በስራ ላይ ባለው አዋጅ ከ30 እስከ 33 በመቶ ይቀረጡ የነበረ ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከ20 እስከ 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጥላል።

ለስላሳ መጠጦችና አልኮል አልባ መጠጦች ውሃን ጨምሮ በስራ ላይ ባለው አዋጅ ከ30 እስከ 40 በመቶ፤ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ከ15 እስከ 25 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጥላል።

አልኮል እና የአልኮል መጠጦች በስራ ላይ ባለው አዋጅ 50 በመቶ የነበረ ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ከ30 እስከ 80 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል ያዛል።

ባለቀለም ቴሌቪዥኖች፣ ቪዲዮ መቅረጫ ወይም ማባዣ መሳሪያዎች፣ የቴሌቪዥን ስርጭት መቀበያዎች፣ ፎቶና ቪዲዮ ካሜራዎች በስራ ላይ ባለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ እስከ 40 በመቶ የሚጥል ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን 10 በመቶ እንደሚሆን ተመልክቷል።

የማዕድን ውጤቶች በስራ ላይ ባለው አዋጅ 30 በመቶ ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መሰረትም ባለበት የሚቀጥል ይሆናል።

ሽቶና መሰል መዋቢያዎች በስራ ላይ ባለው አዋጅ 100 በመቶ ሲሆን፥ በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅም ባለበት የሚቀጥል ይሆናል።

ጨርቃ ጨርቅና ውጤቶቻቸው በስራ ላይ ባለው አዋጅ 10 በመቶ ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ 8 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጣልባቸው ይሆናል።

የተፈጥሮ እንቁዎች፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ በከበሩ ድንጋዮች የተሰሩ ጌጣጌጦች በስራ ላይ ባለው አዋጅ 20 በመቶ ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅም ባለበት ይቀጥላል።

ምንጣፎች ላይም በነባሩ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ 30 በመቶ የሚደነግግ ሲሆን፥ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅም ባለበት የሚቀጥል ይሆናል ነው የተባለው።

በሀይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.