ለ1 ሺህ 400 ዓመታት የአክሱም ስልጣኔ የአስተዳደር ማዕከል የነበረ ከተማ በቁፋሮ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ1 ሺህ 400 ዓመታት የአክሱም ስልጣኔ የአስተዳደር ማዕከል የነበረ ቤተ ሰማዕቲ ከተማ በቁፋሮ ተገኘ።
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት አመታት ቁፋሮ ሲያካሂዱ የነበሩ ተማራማሪዎች ባሳተሙት የጥናት ውጤት ከተማውን በቁፋሮ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
በጥናቱ ከአሜሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ጀርመን፣ ሊባኖስ፣ እንግሊዝ እንዲሁም ካናዳ የተውጣጡ የስነ ምድር ተመራማሪዎች ተሳትፈውበታል።
ተመራማሪዎቹ ቤተ ሰማዕቲ ከተማ የአክሱም ስልጣኔ አስተዳደር ለንግድና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ቀይ ባህርን ለመጠቀም በመዲናነት ይገለገልበት እንደነበር ገልጸዋል።
ቤተ ሰማዕቲ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አህፈሮም ወረዳ መዝብር ቀበሌ ከዕዳጋ ረቡዕ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ቦታ ሲሆን፥ በአከባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ የተለያዩ ቁሶች ያገኙ እንደነበርም ባለሙያዎቹ አመላክተዋል።
ጥናቱ በሁለት ቦታዎች የተከናወነ ሲሆን ከ2011 እስከ 2015 በተከናወኑ ቁፋሮዎች የተለያዩ የህንፃ ፍርስራሶች መገኘታቸው ነው የተገለጸው።
ከዚህ በተጨማሪም ከቤተ ሰማዕቲ ናሙና ተወስዶ በፈረንጆቹ 2015 ይፋ በተደረገው የቤተ ሙከራ ውጤት መሰረት ስንዴ፣ ገብስ፣ የአገዳ አዝዕርትና ከሰል በአካባቢው ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡
ለመኖሪያነት ወይም ለስብሰባ ሲያገለግሉ የነበሩ ጥንታዊ ቤቶች መገኘታቸውም በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ቤተ ሰማዕቲ ለቀይ ባህር ቅርብ በመሆኑ የአክሱም ስልጣኔ ለንግድ፣ ለአስተዳደርና ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ይጠቀምበት እንደነበር መገለጹን ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የተለያዩ የወቅቱን የቴክኖሎጂ ምጥቀት የሚያሳዩ የወርቅ ቅብ ቀለበት፣ በአፄ አርማህ፣ ኢዛናና ሌሎች የአክሱም ስልጣኔ ነገስታት በስማቸው የተቀረፁ የመገበያያ ሳንቲሞች መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ በጥናቱ የተሳተፉት በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ መምህርና ተማራማሪ አቶ ክፍለ ዘርኡ፥ በቤተ ሰማዕቲ ከይሓ ቀጥሎ የቅድመ አክሱም ማሳያ የሆኑ የተለያዩ ቅርሶች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቤት ፍርስራሶች፣ የሸክላ መሳሪያዎች፣ አዝዕርት፣ ሳንቲም፣ እንደ በግ፣ ፍየልና ግመል የመሳሰሉ የቤት እንስሳት ቅሪቶች፣ የብረትና የብርጭቆ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ጥናቱ አሜሪካ በሚገኘዉ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት ተመራማሪው፥ ቀጣይነት እንዲኖረው ለቅርስ ጥናት ፍቃድ የሚሰጡ የመንግስት አካላት እንዲሁም በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።