Fana: At a Speed of Life!

በኮቪድ-19 ተፅዕኖ የተጎዱ የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮችን ለማገዝ በኦንላይን የፎቶ አውደርዕይ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮቪድ-19 ተፅዕኖ የተጎዱ የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮችን ለማገዝ ያለመ ‘የኦንላይን ፎቶ አውደርዕይ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ሆቴልና ማርኬቲንግ ማህበር ገለፀ።
 
ማህበሩ ወደ አፍሪካ የሚገቡ የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መዳረሻ ለሚያደርጉ ‘የቱሪስት ፓኬጅ’ም እያዘጋጀሁ ነው ብሏል።
 
ኑሮአቸውን ጎብኚዎችን በማስተናገድ ብቻ ያደረጉ የቱሪስት መዳረሻዎች አሁን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ”በእጅጉ” መጎዳታቸውን የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታዲዎስ ክንፉ ተናግረዋል ።
 
በዚህም ማህበሩ የዘርፉ ተዋናዮች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች ጋር በመተባበር የኦንላይን አውደርዕይ ለማዘጋጀት እየሰራ ነው ብለዋል።
 
አውደርዕዩን ለማድረግ የሚያስችለው መተግበሪያም 80 በመቶው ሥራው መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ታዲዎስ፤ ለአንድ ዓመት የሚቆየው መተግበሪያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ክፍያውን በመፈጸም በአውደርዕዩን የሚሳተፉበት ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
 
ማህበሩ ባደረገው ጥናት በአውደርዕዩ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።
 
ገቢውም ለመሰረተ ልማት ዝርጋታና ተጎጂዎች ከጉዳታቸው እንዲያገግሙ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ዋና ሥራ አስፈጻሚው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ተፈጥራዊም ሆነ በባህላዊ የመስህብ ሃብቶቿ ቱሪስቶችን ለመሳብ ዕምቅ አቅም እንዳላት ገልጸው፤ ዘርፉን በማስተዋወቅ ረገድ ውስንነት በመኖሩ ተጠቃሚ እንዳልሆነች አመልክተዋል።
 
በዚህም አፍሪካን በየዓመቱ ከሚረግጡ ከ25 ሚሊየን በላይ የውጭ ቱሪስቶች ውስጥ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት አንድ ሚሊየን አይሞሉም ተብሏል።
 
ማህበሩም ምሥራቅ አፍሪካን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ኢትዮጵያንም የሚጎበኙበትን ‘የቱሪስት ፓኬጅ’ የተሰኘ አሰራር እያዘጋጀ መሆኑንና ስራውም 70 በመቶ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
 
በዚህም በተለይም ኬንያን፣ ታንዛኒያንና ደቡብ አፍሪካን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ኢትዮጵያንም የሚጎበኙበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
 
በአዲስ አበባ በመሰራት ላይ የሚገኙ የቱሪዝም ልማት ሥራዎችም ለቱሪስቶች ቆይታ ተጨማሪ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አቶ ታዲዎስ ተናግረዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.