ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳታላይቷን ወደ ህዋ አመጠቀች
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳታላይቷን ወደ ህዋ አመጠቀች ።
ሳታላይቷ ቻይና ከሚገኘው የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ህዋ መጥቃለች።
ምድርን እየቃኘች እና በፎቶ እየመዘገበች መረጃ የምትሰበስበውና “ETRSS-1” የሚል ስያሜን የተሰጣት ሳተላይት በሀገራችን የዕድገት ጉዞ ላይ ቁልፍ ሚና እንደሚኖራት ታምኗል።
በተጓዳኝም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ ጥናት እና ምርምሮችን ለመሥራት እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት ተግባራትን ለማከናወን ታስችላለች ነው የተባለው።
ሳተላይቷ በቻይና ሀገር ውስጥ ከሚገኝ የማምጠቂያ ማዕከል ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ወደ ህዋ የምትመጥቅ ሲሆን በአዲስ አበባ ውስጥም ይህን ታላቅ ታሪካዊ ክስተት የሚዘክሩ በርካታ ዝግጅቶች ከዛሬ ጀምሮ ይከናወናሉ፡፡
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ የፌደራልና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ሳታላይቷን ዛሬ ወደ ህዋ የማምጠቅ ስነ ስርዓትን ከእንጦጦ ስፔስ ሳይንስ ኦብዘርቮተሪ የመከታተል ስነ ስርዓት ተከናውኗል።
በስነ ስርዓቱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ የተወነጨፈችው ETRSS-1 ሳተላይት ለሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ ታሪካዊ መሰረት የምትጥል መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የቴክኖሎጂ ልማት እና ዓለም አቀፋዊ የተወዳዳሪነት ጉዞ መጠናከር እንደሚገባው ተናግረዋል።
ሀገሪቱ የማይቀረውን ዓለም በተወዳዳሪነት በፍጥነት መቀላቀል እንዳለባት በማመልከት፥ ይህ የሳተላይት ጅምር ጉዞ አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ለኛ ለኢትዮጵያውያን . . . ጨለማን እየፈራን ብርሃን የምንናፍቅ” ህዝቦች እንዳልሆንን በተግባር የተረጋገጠበት ታሪካዊ እርምጃ መሆኑ ነው” ብለዋል።
መጪው ዘመን ከየብስ ተሻግሮ በህዋ ሳይንስ ሊኖር የሚገባውን የተወዳዳሪነት አቅም ከወዲሁ መገንባት እንደሚገባ አስምረውበታል።
በሃገራችን የስፔስ ሳይንስ ልማት ጉዞ ለደረሰበት የዕድገት ምዕራፍ ለተረባረቡ ግለሰቦች፤ የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ተቋማት እና አጋር አካላት – ላበረከቱት ታሪካዊ አስተዋጽኦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አመስግነዋል።