ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ እያስከተለ ያለውን ጉዳት እየጎበኙ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ እያስከተለ ያለውን ጉዳት እየጎበኙ ነው።
ከተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን፣ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ከውሃ ልማት ኮሚሽንና ሌሎች ተቋማት የተወጣጡ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በአፋር ክልል ዞን ሶስት አሚባራና አካባቢው ጎርፉ ያስከተለውን ጉዳት ነው እየጎበኙ የሚገኙት።
የጎርፉ አደጋ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የአሚባራ ከተማ ነዋሪዎችን ከአካባቢው ለማስወጣት የተለያዩ ጥረቶች ተጀምረዋል።
በዛሬው እለትም የከተማው ህዝብ መንቀሳቀስ እንዲችል መከላከያ ሰራዊት አራት ጀልባዎችን ይዞ ወደ ከተማዋ ገብቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሄሊኮፕተሮችም በውሃ የተከበቡትን ሰዎች ከአካባቢው በማስወጣት ላይ ናቸው።
የስራ ሃላፊዎቹ የአዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቶ ተፈጥሮአዊ መንገዱን ለቆ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶችን ከጥቅም ውጪ ያደረገበትን ቦታም ጎብኝተዋል።
ሃላፊዎቹ በቀጣይም ወንዙ ያደረሰውን ጉዳት ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘገቧል።
በጎርፉ አደጋ ላይ የወደቁ ዜጎችን የመታደግና አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።