የአብሮነት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአብሮነት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል።
ቀኑ “እኔ ለወገኔ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ሲሆን፥ በዚህም ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጽዮን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎች ጋር የማስ ስፖርት የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ ተጀምሯል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ ዛሬ የአብሮነት ቀን ነው፤ ስለዚህም በአብሮነት ቀን በአንድነት የምንሰራው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በከተማችን ለምናደርገው የጋራ የልማትና የእድገት ጉዞ ጋር መያያዝንና መቀራረብን በመፍጠር መደላደልን የምንፈጥርበት ነው ብለዋል።
በዚህም የከተማዋ ነዋሪዎች በመያያዝና አብሮ በመስራትን አዲሱን ዓመት በተስፋ እና በደስታ እንዲቀበሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
የአብሮነት ቀን ሲታሰብ “እኔ ለወገኔ” የሚል ሀሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር ምክትል ከንቲባዋ በጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚኖሩ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍል ለባዓል የሚሆኑ የማዕድ ማጋራት ስጦታዎችን አበርክተዋል።
እንዲሁም ለተማሪዎች ደግሞ አጋዥ መጽሃፍ እና እንኳን አደረሳችሁ መልእከት የያዘ ካርድን አበርክተዋል።
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ከተማ 700 ሺህ ደቦዎችን በነፃ ለማከፋፈል ቃል የገባው ሸገር ዳቦ ዛሬ ጠዋት ላይ ከ400 ሺህ በላይ ዳቦን ለሁሉም ክፍለ ከተማ ያከፋፈለ ሲሆን፥ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተገኝተው ይህንን መርሃ ግብር አስጀምረዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለበዓል ስጦታ 400 በጎችን በየካ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች አበርክቷል።፡፡
የበዓል ስጦታው ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስረከቡ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች በአብሮነት በመቀራረብና በመተሳሰብ አዲሱን አመት ልቀበሉ ይገባል ብለዋል።
ቀኑ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚቀጥል ሲሆን፥ በየካና እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች መሰል የማዕድ ማጋራት መርሃ ገብሮች በምክትል ከንቲባዋ ይተገበራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፍሬህይወት ሰፊው
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።