Fana: At a Speed of Life!

አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከፈረንሳይና ፊንላንድ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ ከፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንቴምስ ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ሂደት፣ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መክረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሚዲያ ዘርፍ ፈረንሳይ ለጋዜጠኞች ስልጠና በመስጠት እገዛ ማድረግ በምትችልበት አግባብ ላይም ተወያይተዋል።

አቶ ተመስገን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ጥናት በመጠናቀቁ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል።

አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንቴምስ በበኩላቸው በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ባደረጉት ጉብኝት ሠላማዊ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዳለ መታዘባቸውን ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ጎብኝዎች የክልሉን የመስህብ ሀብቶች እንዲጎበኙ ወደ ፊት እንደሚሠራም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

በተያያዘም ርዕሰ መስተዳድሩ በኢትዮጵያ ከፊንላንድ አምባሳደር ህሊና ኤራክሲነን ጋር ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ወቅት በፊንላንድ መንግሥት ድጋፍ በአማራ ክልል እየተከናወኑ በሚገኙ የግብርና፣ የትምህርትና ንጹሕ መጠጥ ውኃ ግንባታ ሥራዎችና በቀጣይ መከናወን ባለባቸው ተግባራት ላይ ነው የተወያዩት።

የፊንላንድ አምባሳደር ህሊና ኤራክሲነን እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ፊንላንድ ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ በግብርና፣ በመሬት አስተዳደርና የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት በጋራ እየሰሩ ነው።

ሀገሪቱ የያዘቻቸውን የልማት እንቅስቃሴዎች ለመደገፍም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የ22 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ መፈራራማቸውንም ጠቅሰዋል።

ክልሉ ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ፊንላንድ አግሮ ቢግ እና ኮ ዋሽ በተባሉ መርሀ ግብሮች እየሠራች ላለው ሥራ ምስጋና አቅርበዋል።

በአግሮ ቢግ በግብርና ፕሮግራም በክልሉ ስምንት ወረዳዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፥ ኮ ዋሽ ደግሞ በንጹህ የመጠጥ ውኃ ተደራሽነት በክልሉ 40 ወረዳዎች እየተሠራበት የሚገኝ ፕሮግራም ነው።

ፊንላንድ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥልና የፊንላንድ ባለሃብቶች በክልሉ በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.