Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለሦስት ዓመታት የሚተገበር የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ማስፈፀሚያ እቅድ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4 2013 (ኤፍ..) በአዲስ አበባ ከተማ ከ2013 እስከ 2015 .ም ድረስ የሚተገበር የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ማስፈፀሚያ እቅድ ይፋ ሆኗል፡፡

ስትራቴጂው በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት በተለይም ከብዙኃን ትራንስፖርት አቅርቦት ጀምሮ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ውስብስብ የትራንስፖርት ስርዓትን በመሰረታዊ መንገድ መቅረፍ የሚያስችል እቅድ ነው ተብሏል፡፡

አዲሱ ማስፈፀሚያ እቅድ በከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት፣ ባለድርሻ አካላት፣ አጋር ድርጅቶች እና ማህበረሰቡ የትራፊክ አደጋን ከመከላከል አንጻር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተነሳሽነትን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተነግሯል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትራፊክ አደጋ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የሁሉም አካል ርብርብ እና ትኩረት እንደሚያሻው ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ሰላማዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ እና የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እና ትኩረት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የትራፊክ ህጎች በአግባቡ እንዲከበሩ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበትና የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂው በወቅቱ ተግባራዊ ተደርጎ ለውጥ እንዲመጣ በፍጥነት ሊሰራ እንደሚገባም ወይዘሮ አዳነች አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ ወይዘሮ አዳነችን ጨምሮ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ፣  የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሳህረላ አብዱላሂ፣ የትራንስፖርት ቢሮና ተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.