የሀገር ውስጥ ዜና

ደቡብ፣ ኦሮሚያና ጋምቤላን በአቋራጭ የሚያገናኘው የጎሬ – ማሻ- ቴፒ መንገድ ግንባታ ተጀመረ

By Tibebu Kebede

December 21, 2019

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ሲጠናቀቅ ደቡብ፣ ኦሮሚያና ጋምቤላን በአቋራጭ የሚያገናኘው የጎሬ – ማሻ- ቴፒ የ140 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ተጀመረ፡፡

ጅማ ፣ ቦንጋ ፣ ሚዛን ቴፒ ፣ ጋምቤላ ፣ ጎሬ ፣ መቱ እና አዲስ አበባን በአጭር ርቅት የሚያገናኘው የጎሬ – ማሻ- ቴፒ መንገድ ግንባታ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት በተገኙበት በዛሬው ዕለት በይፋ ጀምሯል፡፡

ይህ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ በ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደሚከናወን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሮክቶሬት አስታውቋል፡፡

ግንባታውን የደቡብ ኮሪያው ሃዮንዳይ ዴቨሎፕመንት ካምፓኒ የሚያከናውነው ሲሆን የመንገዱን ግንባታ የማማከር እና የቁጥጥር ስራውን ሱሶንግ ኢንጅነሪንግ ከሀገር በቀሉ ኔት ኮንሰልተንግ ኢጅነርስ በጋራ ያከናውኑታል ተብሏል፡፡

የመንገዱ ፕሮጀክት በገጠር 10 ሜትር ፣ በቀበሌ የእግረኛ መንገድ ጨምሮ 12 ሜትር ፣ በወረዳ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 19 ሜትር እና በዞን የእግረኛ መንገድን ጨምሮ  21 ነጥብ 5 ሜትር የጎን ስፋት እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡

የስራ ተቋራጩ በአሁን ወቅት የቅድመ ዝግጅት ስራውን በማጠናቀቀ የግንባታ ስራውን መጀመሩ የተገለፀ ሲሆን  ግንባታው በ4 ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ይጠናቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ባለፈ ይህ የመንገድ ፕሮጀክት  ለአካባቢው ነዋሪዎች ማህበራዊ ፣ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ተጠቁሟል፡፡

በይስማው አደራው