አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል- የአማራ ክልል መንግስት
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ መስጊዶች እና ቤተክርስቲያን መቃጠላቸውን ተከትሎ የክልሉ መንግስት አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንደሚያቀርብ ገለፀ።
በትናንትናው እለት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ መስጊዶች እና ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የክልሉ መንግስት በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው በሰጡት መግለጫ፥ የክልሉን ሰላም የማይሹ ሀይሎች ትናንት ምሽት በመስጊዶች እና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልፀዋል።
በእነዚህ ጥቃቶችም በአምስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ ጌትነት፥ በሰው ህይወት ላይ ግን የደርሰ ጉዳት እንደሌለም አስረድተዋል።
የፀጥታ ሃይሉ ከማህበረሠቡ ጋር በመሆን ተጠርጣሪዎችን ለህገ ለማቅርብ በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በዚህም እስካሁን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው አቶ ጌትነት የገለፁት።
በቀጣይም የፀጥታ ሀይሉ ብህረተሰቡን በማስተባበር አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቁት።
አቶ ጌትነት ይርሳው፥ በትናንትናው እለት በደረሰው ጉዳት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰማውን ልባዊ ሀዘን ይገልፃልም ብለዋል።
በምስራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ለዘመናት በፍቅር የኖሩትን ህዝቦች ለማራራቅ ያለመ መሆኑንምዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል።
ጥቃቱ የሙስሊም እና የክርስቲያን ወንድማማች ህዝቦችን አይወክልም ያሉት አቶ ጌትነት፥ ለዘመናት በፍቅር በመቻቻል እና በመረዳዳት የኖሩት የሁለቱን እምነት ተከታዮች ለማራራቅ የሚጥሩ ሃይሎችም እንደማይሳካላቸው ገልፀዋል።
በናትናኤል ጥጋቡ