Fana: At a Speed of Life!

ቤተ ክርስቲያኗ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ የምስጋና ሽልማት አበረከተች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የምስጋና ሽልማት አበረከተች።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሽልማቱ የተበረከተላቸው ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በቅርበትና በትብብር በመስራታቸው መሆኑም ተገልጿል።

የምስጋና ሽልማቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደተበረከተላቸውም የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች በምስጋና ሽልማት ስነስርዓቱ የተገኙ ሲሆን፥ አስተደዳሪዎቹ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለቤተ ክርስቲያኗ እያሳዩ ላሉት ቀና ትብብርና ድጋፍ ምስጋቸውን አቅርበዋል።

በተለይም ቤተክርቲያኗ ለረጅም አመታት በቅሬታነት ስታነሳቸው የነበሩ ይዞታና ማረጋገጫ ካርታዎችና የተለያዩ ጉዳዮች መፍትሄ እንዲገኙ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተነስቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያኗ በምታዘጋጃቸው መርሀ ግብሮችም ይሁን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በሚከበሩ በዓሎች የከተማ አስተዳደሩ የሚያሳየው ድጋፍና ትብብር በቤተ ክርስቲያኗ ምስጋና ተችሮታል።

ከቀናት በፊትም የከተማ አስተዳደሩ የጥምቀት በዓል በዪኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ በመስፈሩ የተሰማውን ደስታ የገለጸ ሲሆን፥ የመጪው የጥምቀት በዓል በደመቀና የቱሪስቶችን ቀልብ በሚስብ መልኩ እንደከበር የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.