አቶ ልደቱ አያሌው ክስ ቀረበባቸው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ ልደቱ አያሌው የጦር መሳሪያ አስተዳደር አዋጅ 1177/2012 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 3ትን በመተላለፍ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ክስ ቀረበባቸው፡፡
ክሱ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዳማ ከተማ በምስራቅ ሸዋ ዞን ጠቅላይ አቃቤ ህግ የቀረበባቸው ሲሆን በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው ክስ የተመሰረተባቸው፡፡
አቶ ልደቱ ከዚህ በፊት በሰኔ 23 እና 24 በቢሾፍቱ ከተማ አመጽና ሁከት እንዲቀሰቀስ በገንዘብ ሲደግፉና ሲያስተባብሩ ነበር ተብለው ምርምራ ሲከናወንባቸው እንደነበረ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
ይሁንና በዚህ ምርመራ ላይ ፍቃድ የሌላቸው የጦር መሳሪያ አግኝቼባቸዋለሁ በማለት ነው አቃቤ ህግ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ ያቀረበባቸው፡፡
ከሰዓት በዋለው ችሎት በሁለት ዳኛ የተሰየመ ሲሆን አቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ አንብቦላቸዋል፡፡
በክሱ ላይ በሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት በቢሾፍቱ ከተማ ቢልቢላ ፎቃ በሚባል ቦታ በአቶ ልደቱ መኖሪያ ቤት ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ አንድ ሽጉጥ ከአንድ ካርታና ከ16 ፍሬ ጥይት ጋር በፍተሻ መያዙን በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ይህም ህገወጥ ፍቃድ የሌለው መሳሪያ ነው ያለው አቃቤ ህግ ፍቃድ የሌለው መሳሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል መከሰሳቸውን በችሎቱ ተነቧል፡፡
አቶ ልደቱ በሁለት ጠበቆች የተወከሉ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ማንነታቸውን የማረጋገጥ ስራ ሰርቷል፡፡
በዚህም አቶ ልደቱ የሃምሳ ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ መሆናቸውን ቋሚ አድራሻቸው ኮልፌ ቀራንዮ መሆኑንና በንግድ ስራ የሚተዳደሩና ፖለቲከኛ መሆናቸውን መዝግቧል፡፡
በተጨማሪም የመጀመሪያ ዲግሪ እና ሁለት የሁለተኛ ዲግሪ መያዛቸውን በማንነት ማረጋገጥ ምዝገባ ላይ አስመዝግበዋል፡፡
የአቶ ልደቱ ጠበቆች ደምበኛቸው የልብ ህመምተኛ መሆናቸውን በመግለጽ የተሰራላቸው የልብ ቀዶ ጥገና ተከትሎ በሰው ሰራሽ እንደሚገኙና የአስም በሽተኛ መሆናቸውን ከዚህ በፊት መቅረቡን በመጥቀስ አሁንም በጽሁፍ የህክምና ማስረጃ ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡
ህመማቸው ለኮሮና ቫይረስ እንደሚያጋልጥ የጠቀሱት ጠበቆቹ የተከሰሱበት ወንጀል ዋስትና እንደማያስከለክላቸው በማንሳት ዋስትና ተፈቅዶላቸው ህክምናቸውን እንዲከታተሉ የዋስትና ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከሳሽ አቃቤ ህግ ወደ ውጪ ቢወጡ ላይመለሱ ይችላሉ ምስክሮችም ሊሸሹ ይችላሉ ሲል ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡
የሁለቱን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄያቸው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት እና በክሱ ላይ ክርክራቸውን ለመመልከት በይደር ለነገ 4 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
በታሪክ አዱኛ