በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራ ልዑክ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን እየተከናወነ ያለውን የግብርና እንቅስቃሴ እየጎበኘ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሚኒስትሮችን፣ ሚኒስትር ዲኤታዎችን እና የክልሉን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ያካተተ በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራ ልኡክ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን እየተከናወነ ያለውን የግብርና እንቅስቃሴ እየጎበኘ ይገኛል፡፡
በጉብኝቱ በአርሶ አደሩ ቀዬ በከፍተኛ ሁኔታ ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ የሚያስችሉ ስራዎችን በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ልኡኩ በዱግዳ ወረዳ በወር ከ7 ሚሊየን በላይ ችግኞቾን ለአከባቢው አርሶአደሮች የሚያቀርብ ፍሎራ ቫጅ የአትክልትና ፍራፍሬ የችግኝ ጣቢያ እና በክላስተር ተደራጅተው በሄክታር ከ40 እስከ 50 ኩንታል የፓፓያ ምርቶች በሚያገኙ የአርሶአደሮች ቀዬ ላይ ተገኝቶ የስራ እንቅስቃሴውን ጎብኝቷል ።
አርሶ አደሩ በክላስተር ተደራጅቶ የሜካናይዜሽን፣ የገጠር ፋይናንስና የመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ስፋት ያለው የስራ እድልን በመፍጠር እና ከውጪ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት በሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ አየተሰራ መሆኑ ለሚኒስትሮቹ ገለፃ ተደርጓል ።
በዚህም ክልሉ በስንዴ፣ በገብስ ጤፍና መሰል ዋና ዋና ምርቶችን 2ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በክላስተር መሸፈኑ ተገልጿል፡፡
በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የወጪ ንግድ መጠንን ማሳደግ ላይ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡
ክልሉ ይህንን ሲሰራም ምርቶችን በስፋት በጥራትና በፍጥነት ማምረት ላይ ትኩረት አድርጎ መሆኑ ተገልጿል ።
በትዝታ ደሳለኝ