በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግር ተሳተፈዋል የተባሉ 358 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር መዋላቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመተከል ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ተሳተፈዋል የተባሉ 358 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ÷ በቅርቡ በመተከል ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት እናየሕግ የበላይነትን ለማስከበር የክልሉና የፌዴራል መንግስት በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሰሞኑ በመተከል ዞን ቡለን እና ወምበራ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ አየተሠራ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ የተለያዩ ተሳትፎዎችን አድርገዋል የተባሉ ተጨማሪ 30 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አበራ ጨምረው ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች ተሳትፎ የነበራቸው 328 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አበራ÷ሰሞኑን በ2ቱ ወረዳዎች እየተሠራ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ ተጨማሪ 30 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
እስካሁን በተሠራው የህግ ማስከበር ሥራም ለችግሩ መፈጠረና መባባስ የተለያዩ ተሳትፎ የነበራቸው 358 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
ሰሞኑን በዞኑ ወምበራ ወረዳ የጸጥታ ችግር በተፈጠረባቸው ቀበሌዎች 1 የፖሊስ አባልን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ተባባሪ ነበሩ ተብለው የተጠረጠሩ 8 ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
በተመሳሳይ በቡለን ወረዳ ኤጳር፣ አይጋሊና በዶሬ ቀበሌዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግርና ከደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ በቡለን ማዕከል ሆነው ሲተባበሩ የነበሩ 22 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር እንደዋሉ ገልጸዋል።
ከእነዚህም ውስጥ በኤጳር ቀበሌ 13፣ በአይጋሊ ቀበሌ ደግሞ 1 በድምሩ 14ቱ በቀጥታ በግዲያ ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ 4ቱ በቡለን ወረዳ ማዕከል ሲተባበሩ የነበሩ ቀሪዎቹ 2ቱ ደግሞ በቀበሌዎቹ የተለያዩ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ሃላፊው አያይዘውም መንግስት በሁለቱ ወረዳዎች በንጹኃን ዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱ ኃይሎችን ለመደምሰስና በቀጥታም ሆነ በተለያየ መልኩ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ቁጥጥር ስር ለማዋል እየሠራ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቃቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።