የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሞጣ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሞጣ ከተማ በእስልምና እና ኦርቶዶክስ እምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሞጣ ከተማ በእስልምና እና ኦርቶዶክስ እምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት በጥብቅ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።
የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፥ አርብ ዕለት በሞጣ ከተማ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና እና በእስልምና እምነት ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃት እምነት ያለው ሰው የሚፈፅመው ድርጊት አለመሆኑን ገልጿል።
የቦርዱ ሰብሳቢ መልአከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለም፥ የሞጣ ከተማ ህዝብ በፍቅር፣ በአንድነት፣በመቻቻል እና በመተባበር ተከባብሮ የሚኖር መሆኑን አንስተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ክርስቲያኖች የሙስሊም መስጊድ የመስራት በተመሳሳይ ሙስሊሞች ደግሞ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እየገነቡ በመተሳሰብ የሚኖሩ መሆናቸውን አውስተዋል።
ሰሞኑን በሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ የተፈፀመው ጥቃት እምነት ካለው አካል ሊፈጸም የማይችል እኩይ ተግባር መሆኑን የገለጹት መልአከ ሠላም ኤፍሬም ፥ ድርጊቱ በጥብቅ ሊወገዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ቤተ እምነት ሰዎች ችግራቸውንና ደስታቸውን ለፈጣሪያቸው የሚነግሩበት፣ ትምህርት የሚያገኙበት፣ ፍቅር እና ሠላም የሚሰበክበት፣ ሕሙማን የሚፈወሱበት እና የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶች የሚከወኑበት መሆኑን አንስተዋል።
ስለሆነም እነዚህን ተቋማት በእሳት ማቃጠል በምድራዊ እና ሠማያዊ መንግሥት እንደሚያስጠይቅ አስረድተዋል።
መንግስትም በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን አጣርቶ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው አሳስበዋል።
በተያያዘ ዜና በሞጣ ከተማ በቤተ እምነቶች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ 15 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ ተስፋዬ ተናግረዋል።
ከተማዋ በዛሬው ዕለት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሷም ተመላክቷል።
በናትናኤል ጥጋቡ