የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሕግ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ

By Meseret Awoke

September 22, 2020

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሕግ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት በዛሬው እለት ተፈርሟል።

በኢትዮጵያ የሕግ መዝገበ ቃላት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችለውን ፕሮጀክት የፌደራል የፍትህና የሕግ ምርምር እና ስልጠና ኢንስቲትዩት፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ በጋራ በመሆን ለማዘጋጀት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን የሕግ መዝገበ ቃላት እንዳልነበረ የገለፀ ሲሆን ይህም ሁሉም ህብረተሰብ በህግ ጉዳይ ላይ እኩል አረዳድ እንዳይኖር አድርጓል።

የሚዘጋጀው መዝገበ ቃላት በህግ ስርአቱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚፈጥር የፌደራል የፍትህና የሕግ ምርምር እና ስልጠና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ገልጸዋል።

በመዝገበ ቃላቱ ላይ 4 ሺህ 500 ያህል ቃላትን ለመተርጎም የታቀደ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ የሚዘጋጅ ሆኖ በቀጣይ ደግሞ በክልል ቋንቋዎችም እንደሚዘጋጅ ተገልጿል።

በዘመን በየነ