Fana: At a Speed of Life!

የሃይማኖት አባቶች ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንፈሳዊና አባታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የሃይማኖት አባቶች ኤች አይ ቪ/ኤድስን መከላከልና መቆጣጠር ሂደት ላይ መንፈሳዊና አባታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትሯ የሃይማኖት ተቋማት በኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የሃይማኖት አባቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነታቸው የጎላ በመሆኑ ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከልና መቆጣጠር እና የጸረ አይ ቪ ኤድስ መድሃኒትን አጠቃቀ ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ የሃይማኖት አባቶቹ መንፈሳዊና አባታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቫይረሱ በሃገሪቱ ከተከሰተ በኋላ ባለፉት በሁለት አስርት አመታት ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተከትሎ በሃይማኖት ተቋማት ፣ በማህበራት ፣በአጋር ድርጅቶች እና በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተሰራ ስራ የሞት ምጣኔን በ90 በመቶ እንዲሁም አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን 70 በመቶ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

እንደ ሃገር የተገኘው ውጤት ከሌሎች አፍሪካ ሃገራት የተሻለ ቢሆንም አሁን ላይ ከዚህ በፊት የነበረው ተሳትፎ ቀንሷል ተብሏል።

እንደ ሃገር ያለው የቫይረሱ ስርጭት ወደ 0 ነጥብ 9 የሚጠጋ ቢሆንም በጋምቤላ 4 ነጥብ 3፣ በአዲስ አበባ 3 ነጥብ 2፣ በድሬዳዋ 2 ነጥብ 9 እና በሃረሪ 2 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን በከተሞች ያለው ስርጭትም ከፍተኛ መሆኑ ተነስቷል።

የሃይማኖት አባቶች ኤች አይ ቪ/ኤድስ በሃገሪቱ እያስከተለ የሚገኙ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ሁሉም ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንዲሁም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎችም የጸረ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መድሃኒትና ህክምና በአግባቡ መወሰድ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ግንዛቤ መፍጠሩ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል።

በመድረኩ ላይ የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እንዲሁም የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ሰነዱ ተቋማቱ የኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረግ ጥረት ውስጥ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው።

በአለም 32 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሃይማኖት ኢያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.