ሱዳን በዳርፉር በተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ምርመራ ጀመረች
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሱዳን በዳርፉር ግዛት የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ምርመራ መጀመሯን አስታወቀች።
ምርመራው በፈረንጆቹ 2003 በተቀሰቀሰው የዳርፉር ግጭት ወቅት የተፈጸሙ የግድያና አስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን ያካትታል ተብሏል።
ወንጀሉ እንዲፈጸም አድርገዋል የተባሉ የሃገሪቱ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናትም በምርመራው ወቅት ጉዳያቸው የሚታይ ይሆናል።
ምርመራው አስፈላጊ ከሆነ ከሱዳን ውጭ ይደረጋልም ነው የተባለው፤ ይህም የቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው ይሰጣሉ የሚለውን ግምት አጠናክሮታል።
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አልበሽር ፈጽመውታል ባለው የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀለኝነት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያዙ ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።
በፈረንጆቹ 2003 በዳርፉር በመንግስት ደጋፊዎችና በአማጽያን በተፈጠረው ግጭት 300 ሺህ ሰዎች መሞታቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመላክታል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ