Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የባህል ቡድን የሙዚቃ ዝግጅቱን በአስመራ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት የተመራው የኢትዮጵያ የባህል የልዑካን ቡድን የማጠቃለያ ዝግጅቱን ትናንት በአስመራ ሲኒማ ሮማ አቅርቧል።

የኤርትራ የባህል እና ስፖርት ኮሚሽነር አምባሳደር ዘመዴ ተክለ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሰላም እንዲሰፍን የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ዝግጅቱ እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን እንዲሁም በኤርትራ በኩል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ቅርበዋል።

የኢፌዴሪ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው፥ የኤርትራ የባህል ቡድን በኢትዮጵያ አራት ከተሞች የሙዚቃ ዝግጅት ማቅረቡን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በኤርትራ በነበረው ቆይታ በከረን እና ምፅዋ ደማቅ ዝግጅት ያቀረበ ሲሆን፥ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎችን መጎብኘቱንም አንስተዋል።

ይህም ሁለቱ ሃገራት በተለያዩ ዘርፎች ለመተባበር ያላቸውን እድል መገንዘብ ማስቻሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የልዑካን ቡድኑ ተልዕኮ እንዲሳካ የኤርትራ ህዝብ እና መንግስት ላደረጉት ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.