ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ የቆላ ስንዴ በመስኖ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን በስፋት ለማልማት በ3 ሺህ ሄክታር የዘር ብዜት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በቀጣይ ሶስት ዓመታት ውስጥም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ለቆላ ስንዴ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ሚኒስትሩ በበርሃ አንበጣና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በምርት ብክነት ላይ የደረሰው ጉዳት የዳሰሳ ጥናት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የጥናቱ ውጤትም ወደፊት እንደሚገለጽ አስረድተዋል።
መንግስት የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መወሰኑ የምርት ብክነትን ለመቀነስና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ መነሳሳትን እየፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
ዘንድሮ በዘር ከተሸፈነው 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ መሰብሰቡንም ገልጸዋል።
ቀሪው ምርት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት እንዲሰበሰብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።