Fana: At a Speed of Life!

የኮሌስትሮል መጠንን መቀነስ በኋለኛው ዘመን የልብ በሽታ ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ አንድ ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣን የልብ ችግር ለመከላከል ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠንን መቀነስ እንደሚገባ አንድ ጥናት አመላከተ።

አዲስ ይፋ የሆነው ጥናት በኋለኛው ዘመን የሚከሰትን የልብ በሽታና ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ በአመጋገብ ላይ በተለይም የኮሌስትሮል መጠናቸው ከፍ ያሉ ምግቦችን ማስወገድ እንደሚገባ ያመላክታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም እስከ 45 አመት እድሜ ያሉ ሰዎች ጤናማ አመጋገብን መከተልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ ይገባል የሚል ምክረ ሃሳብን ባለሙያዎቹ አቅርበዋል።

እድሜያቸው ከ30 እስከ 85 የሆኑና ከ19 የተለያዩ ሃገራት የተውጣጡ ሰዎችን ያካተተው ጥናት ላለፉት 13 አመታት ሲካሄድ የቆየ ነው።

ጥናቱ የተካተቱ ሰዎችን አኗኗር፣ አመጋገብ፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና መሰል ጉዳዮችን አካቷል።

በጥናቱም እድሜያቸው ከ45 አመት በታች የሆኑ ሰዎች በአብዛኛው በኋለኛ እድሜ ለሚመጣ የልብና ተያያዥ የጤና ችግር ለሚያጋልጡ አጋጣሚዎች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል።

ይህም በዚህ እድሜ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሰዎች አመጋገባቸውን አለማስተካከላቸው መሆኑ ነው የተገለጸው።

ጥናቱ ለሰውነት አላስፈላጊ የሆነና በልብና የደም ቧንቧ ላይ ችግር የሚፈጥር ኮሌስትሮል የሚያዘወትሩ ሰዎች በኋለኛው እድሜያቸው ለልብና ተያያዥ የጤና ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን ያስረዳል።

በተለይም በወጣትነት የእድሜ ክልል ጤነኛ አመጋገብን መከተልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ በኋለኛው ዘመን ከሚከሰት የልብና ተያያዥ የጤና እክል ራስን ለመጠበቅ እንደሚረዳም አስቀምጧል።

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.