Fana: At a Speed of Life!

በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ22 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች ታቅፈዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ከ22 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች መታቀፋቸውን የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታውቋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት በከተማና በገጠር መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ነው፡፡

ይህ የጤና መድህን ዓይነት በ2003 ዓ.ም በ13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ በትግራይ፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ተጀምሮ ከሙከራ ወረዳዎች የተገኘውን ልምድ በመቀመር ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚዛን ኪሮስ በዛሬው ዕለት በሰጡት  መግለጫ ፥በ2011 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እንቅስቃሴ በ5 ክልሎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር በሚገኙ 657 ወረዳዎች ተጀምሮ 509 ወረዳዎች ቅድመ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ለአባላቶቻቸው የህክምና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

በእነዚህ ወረዳዎች የሚኖሩ ከ22 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚልቁ ዜጎችም በጤና መድህን ስርዓቱ ታቅፈዋል ነው ያሉት።

በጤና መድህን ስርዓቱ ከታቀፉት ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ዓመታዊ የጤና መድህን ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉ ከ5 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና መድህን ወጪያቸው በመንግስት እንዲሸፈንላቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት ከአባላት መዋጮ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የገለጹት ዳይሬክተሩ ፥ የጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦቻቸው በጤና መድህኑ ላገኙት የህክምና አገልግሎት ከ617 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙንም ገልጸዋል።

የ2012 የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት የአባልነት ምዝገባና ዕድሳት መርሃግብር ከታህሳስ ወር ጀምሮ በመከናወን ላይ የሚገኝ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የአባልነት ምዝገባና የዕድሳት ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊትም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተግባራዊ በተደረገባቸው ክልሎች የሚገኙ ዜጎች ለጤና መድህን አባልነት የሚጠበቀውን ዓመታዊ መዋጮ በመክፈል እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና መድህን አባል የሆኑ ዜጎችም አባልነታቸውን በማደስ እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን ከኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓት ትግበራ ስኬት ከፍተኛ ሚና ያላቸው ክልሎች፣ የጤና ሴክተር ባለድርሻ አካላት፣ ዞኖችና ወረዳዎች ነዋሪዎቻቸውን በጤና መድህን ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመሩትን የንቅናቄ ዘመቻ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዘቢብ ተክላይ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.