የ2012 ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን ለማከናውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ቦርዱ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ2012 ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን ለማከናውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለፀ።
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባል ወይዘሪት ብዙወርቅ ከተተ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ቦርዱ በህግ፣ በተቋማዊ መዋቅር፣ በሰው ሃይል፣ በምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦት ዘርፍ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።
አንዲሁም በአዲስ የተደራጀው ቦርዱ ተቋማዊ መዋቅሩ ከሚኖረው ሰራተኛ ብዛትና ብቃት በመፈተሽ ተቋማዊ ሪፎርም ማከናወን፤ በሌላ በኩልም ዋንኛው ስራ የሆነው ምርጫን ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ገቢራዊ የማድረግ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለውን ስራ በመከወን ላይ ነው ብለዋል ወይዘሪት ብዙወርቅ።
በቅርቡ ከተደረገው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ልምድ በመውሰድም የምርጫ ጣቢያዎችን ካርታ የማዘጋጀትና በቁጥርና በመንደር የመጠሪያ ስያሜ ያላቸውን ጣቢያዎች ወጥነት ወዳለው ስያሜ እንዲመጡ እየተደረገ ይገኛል።
አዲስ የወጣውንም የምርጫ ህግ ተከትሎ ቦርዱ ስራውን የሚያከናውንባቸው ከ20 በላይ መመሪያዎችን የተዘጋጁ ሲሆን፥በቀጣይ ሳምንትም ውይይት ይደረገባቸዋል ነው ያሉት።
በያዝነው ዓመት ለሚደረገው ምርጫ ከ250 ሺህ እስከ 300 ሺህ ሰዎች በምርጫ አስፈፃሚነት የሚሳተፉ መሆኑንም አንስተዋል።
እነዚህን የምርጫ አስፈፃሚዎች ከመመልመል አንስቶ እስከ ማስልጠን ያለው ሂደት ተግባራዊ የሚደረግበት አቅጣጫ መንደፍም ሌላኛው የምርጫ ቦርዱ የዝግጅት አካል ሆኖ ተተግብሯል።
በዚህም ለምርጫ አስፈፃሚዎች ከዚህ ቀደም ከሚሰጠው ስልጠና በበለጠ መልኩ ይዘቱን በመጨመር እና ጊዜን በመውሰድ በምርጫ ህጉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ግብ ተቀምጧል።
ከዘጠኙ የክልል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ለስድስቱ ክልሎች ሃላፊዎች በመቅጠር በምርጫ ህጉ ዙሪያ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉም ተገልጿል።
ለቀሪዎቹ ሶስት ክልሎችም ሃላፊዎችን የመመደብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት ወይዘሪት ብዙወርቅ።
በአጠቃላይ ቦርዱ የ2012 ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን ለማከናውን ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ነው የገለፁት።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ድጋፍ አማካኝነት የመራጮች መመዝገቢና የተወሰኑ ለድምፅ መስጫየሚያገለግሉ ህትመቶች ግዥም ይሄን የሚያመለክቱ ነው።
ቦርዱ ወደ 48 ሺህ የሚጠጉ የምርጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት እቅድ ቢኖረውም፤ ከሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ልምድ በመነሳት 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ለመጠባበቂያ የቁሳቁስና የህትመት ግዥ ውል ፈፅሟል።
ይህም አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎቹን 50 ሺህ 900 በማሳደግ ምርጫውን ለማከናውን የሚያስችል ነው።
የቦርዱ ሰብሳቢ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ይህ 9 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገበት የምርጫ ቁሳቀሱ ህትመትን በዘጠኙ ክልሎች 5 የስራ ቋንቋዎች ህትመቱ ተጀምሯል ነው ያሉት።
በቀጣይም የሁለተኛው ዙር ዝግጅት ላይ ለድምፅ መስጫ የሚውሉ የቁሳቁስና ህትመት ግዥ የመፈፀም ተግባር ይከውናል።
በበላይ ተስፋዬ