Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፍሬወይኒ መብራህቱን ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሲ.ኤን.ኤን የ2019 የዓመቱ ጀግና ፍሬወይኒ መብራህቱን በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋገሩ።

በዚሁ ወቅትም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ ፍሬወይኒ መብራህቱ የሲ.ኤን.ኤን የ2019 የዓመቱ ጀግና በመሆኗ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸውላታል።

ፍሬወይኒ በፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ለተደረገላት አቀባበል በማመስገን የተሰማትን ደስታ ገልፃለች።

ሴቶች የተመቻቸ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ውጤታማ የማይሆኑበት ምክንያት እንደሌለ የገለፀችው ፍሬወይኒ፤ የ2019 የሲ ኤን ኤን ጀግና ሆና እንድትመረጥ ላደረጉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ምስጋና አቅርባለች።

ማሪያም ሳባ የተሰኘ የፅዳት መጠበቂያ ምርት የሚያመርት ፋብሪካ በመቐለ ያቋቋመቸው ፍሬወይኒ መብርሃቱ ፥ በዚህ ስራዋም ነው የሲ ኤን ኤን የ2019 ጀግና በመሆን የተመረጠችው።

ከህይወት ልምዷ በመነሳት የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ያቋቋመች ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2006 በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል የንፅህና መጠበቂያ የባለቤትነት ማረጋገጫ በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተሰጥቷል።

ይህ የንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ፋብሪካ ለ42 የአካባቢው ሴቶች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፥ በየአመቱ የወር አበባ መጠበቂያን ጨምሮ 600 ሺህ የንፅህና መጠበቂያ እና 300 ሺህ የውስጥ ሱሪዎችን ያመርታል።

ፋብሪካው ሴቶች በኢኮኖሚው ራሳቸውን እንዲችሉ ወሳኝ ነው ያለችው ፍሬወይኒ መብርሃቱ፥ ለሴት ሰራተኞቿ ነፃ ስልጠና፣ የቴክኒክ ስልጠና ክፍያ እና ሌሎች እድሎችን ይጠቀማሉ ብላለች።

ከዚህ ባለፈ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የንፅህና መጠቢያ መጠቀም እንዳለባቸው በማስተማር የወር አበባ መጠበቂያ ድጋፍ ታደርግላቸዋለች።

በፋብሪካው ከሚመረቱ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ 80 በመቶውን ለሴቶች በነፃ ለሚያከፋፍሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደምትሸጥም ተነግሯል።

በራሀዋ መብራህቱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.