በሀረሪ ክልል የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በሀረሪ ክልል እየተከናወነ የሚገኘውን ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በክልሉ የተካሄዱ ህገ-ወጥ የቤት ግንባታዎችንና የመሬት ወረራ ለማስመለስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል፡፡
የሀረሪ ክልል የከተማ ልማት፣ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልሃኪም አብዱልማሊክ ፥በክልሉ ህግን የማስከበር ክፍተት በመኖሩ ምክንያት መሬት በህገ-ወጥ መንገድ እየተወረረና ህገ-ወጥ ግንባታ በሰፊው እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በአሁኑ ወቅት 10 ሺህ የሚጠጉ ህገ-ወጥ ቤቶች መገንባታቸው እና 150 ሄክታር መሬትም በህገ-ወጥ መንገድ መያዙንም አንስተዋል ፡፡
በተለይም ትምህርት ቤቶች የእምነት ቦታዎች እና ሃኪም ጋራ እንዲሁም ጀጎል ዙሪያ ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ በስፋት ከተካሄደባቸው አካባቢዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡
የአለም ቅርስ በሆነው ጀጎል ግንብ ዙሪያ የተካሄደው ህገ-ወጥ ግንባታ በአፋጣኝ መፍትሄ ካላገኘም ቅርሱን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል 33 ሄክታር ስፋት ያለው ሴላት ፓርክ ሙሉ በሙሉ በህገወጥ መንገድ መያዙ ተጠቁሟል፡፡
የተካሄዱ ህገ-ወጥ ግንባታዎችንና የመሬት ወረራ ለማስመለስና ለመከላከል በክልሉ ከሚገኙ የፀጥታ አካላትና ከወረዳዎች ጋር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ኢክራም ዚያድ በበኩላቸው፥ የክልሉ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከባለፈው አመት አንፃር መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች መሬት በህገ ወጥ መንገድ በመወረሩ ምክንያት ስራ ማቆማቸውንና ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሄዳቸውንም ገልፀዋል፡፡
ይህንና እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ለባለሃብቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ግበረ ሃይል ተቋቁሞ በክልሉ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ህገ-ወጥ ግንባታ የተካሄደባቸው ቦታዎችን ተለይተው ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን በሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ለታ በዳዳ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደትም 159 በሚሆኑ ህገ ወጥ ግንባታዎችና ይዞታዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡