Fana: At a Speed of Life!

በፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ትግበራ ላይ የሚመክር ጉባኤ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ስራ ትግበራ ላይ የሚመክር ጉባኤ በአዳማ ከተማ ተካሄደ።

ጉባኤው በመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ፕሮግራም ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራትን በስፋት የገመገመ ሲሆን፥ በመረጃ ተደራሽነት በኩል በፌደራል፣ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች የተሰሩ ስራዎች ላይ ዳሰሳ አድርጓል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክትር አቶ ዳዊት ሽመልስ የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ስራ ሀገሪቱ ዘመናዊነትን የተላበሰ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖራት ያስችላል ብለዋል።

የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት ከመተግበሩ በፊት በተደረገ ቅድመ ዳሰሳ ጥናት የዜጎች የመረጃ ተደራሽነት አንድ ከመቶ እንዲሁም የተሳትፎ መጠን ደግሞ ስድሰት ከመቶ በታች እንደነበር ተገልጿል።

እንዲሁም ዜጎች በመንግስት በጀት ሂደት ላይ ያላቸው ግንዛቤ ዘጠኝ ከመቶ ብቻ መሆኑም ተጠቅሷል።

በ2009 በጀት ዓመት በተደረገ የአፈጻጸም ዳሰሳ ጥናት መሰረት የዜጎች የመረጃ ተደራሽነት 50 በመቶ የተሳትፎ መጠን ደግሞ 73 በመቶ ሲሆን፥ በመንግስት በጀት ሂደት ላይ ያላቸው ግንዛቤ 67 ከመቶ መድረሱን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.