Fana: At a Speed of Life!

የእስራኤል የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል በማቋቋም የቴክኖሎጂ እውቀት ሸግግር ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 15፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)የእስራኤል የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል በማቋቋም የቴክኖሎጂ እውቀት ሸግግር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  አስታወቀ፡፡

እስራኤል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጉብኝት ወቅት ለመደገፍ ቃል የገባቻቸው ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ለመግባት በሚቻልበት  ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ የተመራ ልኡክ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመስኖ ልማት እና የአሳ እርባታ በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ውይይት አድርገዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር÷የእስራኤል የቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል በማቋቋም ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የቴክኖሎጂና የእውቀት ሸግግር ለማድረግ እንደሚሰራ  ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የስራ እድልና ሃብት ለመፍጠር  ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

እስራኤል ከዚህ ቀደም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሳ ሃብት ልማት፤ የበረሃማ ቦታዎች ልማት፤ የበይነ መረብ ደህንነትና ለቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን በመፍጠር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷ ይታወሳል፡፡

እስራኤል በበረሃማ ቦታዎች ልማትና በትንሽ ቦታ ሰፊ የአሳ እርባታን በማከናወን ሰፊ ልምድ ያላት ሀገር በመሆኗ ሰርቶ ማሳያ በማከናወን ለኢትዮጵያ ለማስረከብ እንቅስቃሴ  መጀመሩም ተገልጿል፡፡

በሰርቶ ማሳያው መሰረትም የኢትዮጵያ መንግስት የማስፋፋቱን ስራ የሚያከናውን ይሆናል።

ፕሮጀክቱ በእስራኤል መንግስስት፣ የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታው አካላት ትብብር ወደ ተግባር የሚገባ  መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.