Fana: At a Speed of Life!

የአማራ እና ትግራይ ህዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ  የውይይት መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ እና ትግራይ ህዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ  የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄደ ።

በውይይት መድረኩ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

መድረኩ “ህብረ-ብሄራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር ውስጣዊ ችግሮቻችንን በምክክር እንፍታ!” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው፡፡

በውይይት መድረኩ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ከሚለያዩባቸው ጉዳዮች ይልቅ የሚያስተሳስሯቸው እና የሚያጣምሯችው የአንድነት ታሪኮች እና ጉዳዮች ጎልተው የሚታዩ መሆኑ ተነሰቷል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በውይይት መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የአማራና ትግራይ ህዝቦች በባህል፣ በሃይማኖት እና ቋንቋ የተሳሰሩ ከመሆናቸው በላይ ሀገር በመገንባትና በመጠበቅም ታሪካዊ አንድነት ያላቸው መሆኑን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይና አማራ ክልል ህዝቦች መካከል የተፈጠረ ችግር አለመኖሩንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።

ይሁን እንጂ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ ጥቅም ፈላጊ ፖለቲከኞችና የማህበራዊ ለውጥ አራማጆች መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አለመግባባቶች መኖራቸው ነው የተገለጸው።

እነዚህ ችግሮች እያደጉ ሄደው በህዝቡ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩም ከጅምሩ በውይይት መፍታት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት በበኩሉ ፥ የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች ሰላም በፍቅር እና እንድነት ለመላ ሀገሪቱ ህዝቦች ህብረት እና አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጿል።

የመማክርቱ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ፥ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ በዘላቂነት ለማስቀጠል ሁሉም የበኩሉን ድረሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጠላት በሌለበት ቦታ ሰይፍ መማዘዝ አያስፈልግም ያሉት ፓስተር ዳንኤል፥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመገናኛ ብዙሃን፣ ምሁራንና ማህበራዊ አንቂዎች የህዝቦችን ልዩነት የሚያሰፉ ዘገባዎችን ከመስራት በመቆጠብ የጋራ እሴቶች ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።

የሀገር ሽማግሌዎችም በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚስተዋሉ ውስጣዊ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ መስራት እንደሚገባቸው ተመላክቷል።

የውይይት መድረኩን የሰላም ሚኒስቴር ከጀስትስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሽፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል።

ባሳለፍነው ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች የተውጣጡ ምሁራን የሁለቱን ክልሎች ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል።

በመሀመድ አሊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.