People hold banners as they demonstrate on the street to protest against police brutality, in Lagos, Nigeria, Tuesday Oct. 20, 2020. After 13 days of protests against police brutality, authorities have imposed a 24-hour curfew in Lagos, Nigeria's largest city as moves are made to stop growing violence. (AP Photo/Sunday Alamba)

ዓለምአቀፋዊ ዜና

በናይጀሪያ እስካሁን 51 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ገለጹ

By Tibebu Kebede

October 24, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ከሰሞኑ በሃገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት 51 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንቱ የፖሊስን የሃይል እርምጃ በመቃወም በተካሄደው ሰልፍ ላይ የፀጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ በርካቶች መቁሰላቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ 11 የፖሊስ አባላት እና ሰባት ወታደሮችም ለህልፈት ተዳርገዋል ነው ያሉት፡፡

በሃገሪቱ ያለውን ሁኔታ እየተከታተሉ ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ደግሞ የፀጥታ አካላት ሰልፈኞች ላይ በመተኮስ በጥቂቱ 12 ንጹሃንን ገድለዋል ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

ቡሃሪ ከአሁን እና የቀድሞ ባለስልጣናት ጋር በሃገሪቱ ከተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ለመምከር በተቀመጡበት ወቅት በሰጡት መግለጫ በጥቂቱ 37 ንጹሃን መቁሰላቸውንም ተናግረዋል፡፡

በስብሰባው ወቅት በሰጡት መግለጫ ፕሬዚዳንቱ በፀጥታ አካላት የተወሰደውን እርምጃ አለማውገዛቸውም ነው የተሰማው፡፡

በወቅቱ መንግስት ህግና ስርአትን እንደሚያስከብርና ስርአት አልበኝነትን አይፈቅድም ማለታቸው የሃገሬውን ዜጎች አላስደሰተም፡፡

በናይጀሪያ የፀጥታ አካላት በሚወስድት ያልተመጣጠነ እና አሰቃቂ እርምጃ ሳቢያ ተደጋጋሚ ትችት ይቀርብባቸዋል፡፡

ከሰሞኑም ይህን የሚኮንን ሰልፍ የተጠራ ሲሆን፥ ተቃውሞው ወደ አመጽና ብጥብጥ እየተቀየረ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡

ምንጭ፥ አልጀዚራ