የወራቤ ቦዣ በር የአስፓልት መንገድ ግንባታ በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የወራቤ ቦዣ በር 40 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በዛሬው እለት በይፋ ተጀመረ።
የመንገድ ፕሮጀት ግንባታ የማስመጀር መርሃ ግብር ላይ የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል፣ የክልልና የዞን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሁለተኛው የመንገድ ዘርፍ አካል የሆነው የወራቤ ቦዣ በር የአስፓልት መንገድ ግንባታ በ795 ሚሊየን ብር ግንባታው የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፥ ግንባታው በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ነው የተባለው።
የወራቤ-ቦዣበር መንገድ ፕሮጀክት የጎን ስፋት የመንገድ ትከሻን ጨምሮ ወትና 21 ነጥብ 5 ሜትር ፣ በቀበሌ 12 ሜትር ሲሆን በገጠር 10 ሜትር ነው መሆኑም ታውቋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ተገንብቶ በሚጠናቀቅበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙና እንደ ጤፍ ፣ በቆሎ ፣ ማሽላ ያሉ የሰብል ውጤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶችንና የቁም እንስሳትን ወደ ማዕከላዊ ገበያ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ያስችላል ተብሏል።
በሌላ በኩል በመስመሩ የሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎችን በአስፋልት መንገድ በቅርበት በማስተሳሰር የትራንስፖርት ጊዜን በማሳጠር ለህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በይበልጥ እንዲያሳድጉ እድል ይፈጥርላቸዋል።
ከዚህም ባለፈም ዋና መንገድ የሆነውን አዲስ አበባ – ሆሳዕና መንገድ ከቡታጅራ ጉብሬ መንገድ ጋር በቅርበት ያስተሳስራል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ ተጀምሮ በአቅም ማነስ ምክንያት የተቋረጠ እንደነበረም ይታወሳል።
በለይኩን ዓለም