Fana: At a Speed of Life!

የቅኝ ግዛት መንፈስ የተጠናወተው የፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግር እና የፈርዖኖች ሩጫ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈርዖኖች ከአሁን በፊት በዓለም ባንክ አሁን ደግሞ በቢሊየነሩ ፕሬዚዳንት በኩል መጥተዋል። የዓባይ (ናይልን) ውሃ የመጠቅለል ዲፕሎማሲያቸውን በትናንት ሁነት ለማንበር እየተሯሯጡ ነው።

አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያን ወዳጆች አስቆጥቷል። በፍትህ የሚያምኑ ሀገራት፣ ፖለቲከኞች፣ ዲፕሎማቶች እና ምሁራን ተንታኞች ደግሞ የፕሬዚዳንቱን እብሪት የተሞላበት ንግግር ሲሰሙ ፕሬዚዳንቱን ምን ነካቸው እያሉ ነው።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ላይ ለግብፅ ያሳዩት ውግንና

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በህዳሴው ግድብ የተሳሳተ አቋም እና አካሄድ መከተል የጀመሩት አሁን ሳይሆን ሃራቸው በግድቡ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር ከዓለም ባንክ ጋር ታዛቢ ሆና በቀረበችበትና ድርድሩ በዋሽንግተን መካሄድ በጀመረበት ወቅት ነበር፡፡

ትራምፕ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት እና ጉዳዩን እንዲይዙት ያደረጓቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አካሄድም ከራሳቸው ሀገር ህገ መንግስት ጋር ሳይቀር የተጣረሰ ነው፤ የታዛቢነቱ እና አሸማጋይነቱን ሚና መወጣት የነበረባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንጅ የገንዝብ ሚኒስትሩ አልነበሩም።
ይህን የትራምፕ ስህተት ከአሜሪካ ህገ መንግስት አንቀፆች አንጻር መሰረት በማድረግ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና የገንዘብ ሚኒስቴር የኮንግረንሱን ማቋቋሚያ አዋጆች መመልከት ያስፈልጋል።

በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የዓለም አቀፍ ህግና የህገ መንግስት ጉዳዮች ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም አሜሪካ በአባይ ጉዳይ እያሳየችው ያለው አቋም ከራሷ ህገ መንግስት ጋር የሚጋጭ መሆኑን በስፋት አትተው ፅፈዋል፡፡

በፈረንጆቹ ሐምሌ 20 ቀን 1789 በኮንግረንሱ የተቋቋመው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተሰጡት ሃላፊነቶች መካከል አሜሪካ ከማንኛውም የውጭ ሀገራት ሚኒስትሮች እና ዲፕሎማትና ባለስልጣኖች ጋር የምታደርገውን ውይይት በበላይነት ይመራል የሚለው ይገኝበታል፡፡
በአንጻሩ መስከረም 2 ቀን 1789 የተቋቋመው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር የአሜሪካን ገቢ ለማሻሻል ህጎችን ማርቀቅ እና ገቢ መሰብሰብ ከተሰጡት ሃላፊነቶች መካከል ዋነኛው እና ቀዳሚው ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ይህን እያወቁ አልያም ሆን ብለው ኢትዮጵያ ላይ የእርዳታ ዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር ድርድሩን የገንዘብ ሚኒስትራቸው እንዲይዙት አደረጉ። ይህ የትራምፕ ቀዳሚ ስህተት እና በግልፅ የውግንና አካሄድ የመከተላቸው ጅማሮም መደምደሚያም ተደርጎ የሚወሰድ ነበር።

ዓለም አቀፍ ህጎችን እና መርሆዎችን የጣሰው አዲሱ የትራምፕ ንግግር

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ላይ ጦርነት እንዲታወጅ የሚያደርግ አስተያየት ሰንዝረዋል። ይህ ደግሞ ለዓለም ሰላም እና ደህንነት የተቋቋሙ የድድርጅቶችን መርህ እና ሀገራቸው የፈረመቻቸውን ህጎች በአደባባይ የሳቱ መሪ አድርጓቸዋል፤ በእርግጥ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓለም አቀፍ ህግን መጣስ አዲስ አይደለም።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህሩ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እየተከታተሉ ያሉት አቶ ደጀን የማነ የትራምፕ አስተያየት ላለፉት ወራት በእርሳቸው ሰዎች እና በዓለም ባንክ ሲደረግ የነበረው ጫና እና መግለጫ ማጠቃለያ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ንግግራቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መመስረቻ ቻርተርን የጣሰ መሆኑን በማብራራት፡፡

ትራምፕ ያደረጉት ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር የተመድን ቻርተር አላማዎችን እና መርሆዎችን የጣሰ በመሆኑ ፕሬዚዳንቱ ሐገራት የዓለም አቀፍ የሰላምና ደህንነት ስጋት ከመሆን እንዲርቁ፣ ከወረራ እንዲታቀቡ እና ፍትህንና የዓለም አቀፍ ህግን መሰረት አድርገው አለመግባባቶችን እንዲፈቱ ከሚያዘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሰረታዊ ዓላማ ያፈነገጠ ንግግር አድርገዋል ነው የሚሉት የህግ መምህሩ አቶ ደጀን።

ከዚህ ባለፈም በሐገራት መካከል በህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ወንድማማቻዊ ግንኙነት (friendly relations) እንዲኖር የማስቻል ዓላማን የተቃረነ ነውም ይላሉ የትራምፕ ንግግር።

የፕሬዚዳንቱ ንግግር የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዓላማዎች መቃረን ብቻ ሳይሆን ዓላማዎችን ለማስፈጸም የተቀመጡ መርሆችንም የጣሰ ነው። በግልፅ ለግብፅ በኢፍትሃዊ አካሄድ እና ጥያቄ በመወገን የሐገራት ሉዓላዊ እኩልነት መርህን ጥሷል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተመድ ቻርተር አንቀፅ 2(4) ላይ የተቀመጠውን የሌሎች ሐገራትን ግዛታዊ አንድነት ወይም ፖለቲካዊ ነፃነት በሀይል የመጠቀም ዛቻ ከማድረግ የመቆጠብ ግዴታን የሚጥለውን መርህ ተላልፈው ግብፅ የኢትዮጵያን ግድብ ልታፈርስ ትችላለች ብለዋል።

የህግ መምህሩ እንደሚናገሩት ይህ የትራምፕ አካሄድ በርካታ ዓለም አቀፍ መርሆችን እና ህጎችን የጣሰ ነው። ሌላው ትራምፕ የጣሱት ህግ የአንዲትን ሉዓላዊት ሀገር መብት በመጋፋት የተፈጥሮ ሃብቷን ሌላ ሀገር ይገባኛል የሚል ጥያቄ እንዲያነሳበት ያውም በሃይል መናገራቸው ነው፤ ካይሮ ትጠቀምበት ያሉት ወንዝ ዓባይ የሚፈሰው ከኢትዮጵያ እንጂ ከግብፅ ባለመሆኑ።

የህግ ጉዳይ ባለሙያው ትራምፕ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚገዛውን የቬናውን የ1969ን ስምምነት ጥሰዋል። ይህ ስምምነት ሐገራት አንድ ስምምነት ውስጥ ለመግባት የድርድሩን ሂደት ለመቆጣጠር እና የድርድሩን ውጤት ለመቀበል በራሳቸው መልካም ፍቃድ ብቻ እንዲወስኑና ይህም የሉዓላዊነታቸው መገለጫ እንደሆነ ይደነግጋል።

ትራምፕ ግን ከዚህ በተቃራኒው ኢትዮጵያ በእርሳቸው ሰዎች የተዘጋጀውን አስገዳጅ ህግ ለማስፈረም ዝተዋል።

ትራምፕ ለአፍሪካ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት የቅኝ ግዛት ዘመን እሳቤን ዳግም የመመለስ ዝንባሌ ይሆን ይሆን?

ትራምፕ ሁልጊዜም ለአፍሪካ የሚሰጡት ግምት የተሳሳተ ነው፤ የግድቡ ድርድር በተጀመረበት ወቅት ካነሱት ሃሳብ ባለፈ አሁን ላይ ግድቡ በአፍሪካ አሸማጋይነት ተመልሶ ሳለ እኔ ካልሆንኩ በሚል ራስ ወዳድ አካሄድ ለአፍሪካውያን አሸማጋዮች የሰጡት ቦታና ግምት በርካቶችን ያስቆጣ ነው።

አቶ እንዳለ ንጉሴ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው።
የትራምፕ አካሄድ ቀጠናዊ ትብብር ከማምጣት ይልቅ አፍራሹን እና ለግጭት የሚዳርገውን የቅኝ ግዛት ዘመን እሳቤ የሚመልስ ነው ይሉታል። የዲፕሎማሲ ጉዳይ አጥኝው እንደሚሉት የካይሮ ሰዎችም ከዚህ የቅኝ ግዛት መንፈስ እሳቤ አልወጡም፤ አፍሪካውያንም ይህን ጊዜ ያለፈበትን እሳቤ በጋራ ለመዋጋት መነሳት ይገባቸዋል ነው የሚሉት።

አያይዘውም ትራምፕ የአፍሪካ ህብረት ያስቀመጠውን አፍሪካውያን የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው ይፍቱ የሚለውን የሚለውን አህጉራዊውን አጀንዳ 2063ንም አጣጥለዋልም ይላሉ፡፡

የተግባቦት እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ እና በሩሲያ የአፍሪካ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዘነበ ክንፉ በበኩላቸው አፍሪካውያን አሁንም ሄድ መለስ የሚለውን የቅኝ ግዛት ዘመን እሳቤ ለማክስም ከተናጠል አካሄድ ይልቅ ትብብራዊ የዲፕሎማሲ መንገድን መምረጥ እንደሚገባቸው ይሄው የትራምፕ እና የዓለም ባንክ አካሄድ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ምሁሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ተሾመ አበበ ደግሞ አፍሪካ በእርዳታ ዲፕሎማሲ ስም ሉዓላዊነቷን አሳልፋ እንዳትሰጥ መጠንቀቅ ያሻታል ነው የሚሉት።

እርሳቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአፍሪካውያን አዲስ ተሞክሮ ይዞ የሚመጣ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል ባይ ናቸው።

እስካሁን በአፍሪካ የተሰሩ ትላልቅ ግድቦች የእርዳታ ዲፕሎማሲ ተፅእኖ ያረፈባቸው ናቸው። የኢትዮጵያው ግን በራስ አቅም እየተገነባ ያለ ክፍለ አህጉራዊ የምጣኔ ሀብት ትስስር የሚፈጥር ፕሮጀክት ነው።
ከአሁን በፊት ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ባለመውደቅ ለአፍሪካውያን የነፃነት አብዮት ለኳሽ የሆነችበትን የፓን ኢትዮጵያኒዝም በኋላ ላይም የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ዳግም በምጣኔ ሀብት በተለይም በግድብ ፖለቲካ መድገም አለባት እነርሱም ከእርዳታ ዲፕሎማሲ ወጥተው ይህን አዲስ የተስፋ ጮራ ማየት ይኖርባቸዋልም ይላሉ፡፡

የፈርዖኖችን የእጅ አዙር ጦርነት ለማክሰም ምን መደረግ አለበት?

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር ተፈሪ መኮንን መፍትሄው የህዳሴውን ግድብ ኢትዮጵያውያን ከኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት የዘለለ ፋይዳ እንዳለው ከመረዳት ይጀምራል ባይ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለጻ እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጠሩ ግጭቶች እና በንጉሱ ዘመንም ይሁን በደርግ አሁን ላይም የግብፅ ስውር እጆች ይታያሉ።

እነዚህን የካይሮ ስውር እጆች መቁረጥ የሚቻለው ደግሞ ግድቡ የሰላም እና የደህንነት ዋስትና ነው የሚል እምነት ከማሳደር ሲጀምር መሆኑንም ያስረዳሉ።

በዓባይ ውሃ ጂኦ ፖለቲካ ላይ የነቃ ተሳትፎ ያላቸው እና በቅርቡም አንድ መፅሃፍ እያዘጋጁ ያሉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ውብእግዜር ፈረደ እንደሚናገሩት ከሆነ ደግሞ የካይሮ ሰዎች የእጅ አዙር ጦርነት የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ልዩነቶችን በማስፋት ብቻ የተገደበ አይደለም።

እርሳቸው ግብፅ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ያልፀናባቸውን ጎረቤት ሀገራት በመጠቀም የሴራ ፖለቲካዋን ልታራምድ ትችላለችና ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ነው የሚሉት፤ የፈርዖኖችን የ1958 በሱዳን ላይ የሰሩትን የሴራ ፖለቲካ እና በእነርሱ ድጋፍ የተቀነባበረውን መፈንቅለ መንግስት በማስታወስ።

መደረግ ያለባቸው አዋጭ የጥንቃቄ ስራዎች ከመንግስት ይጀምራል። አሁን ላይ እዚህም እዚያም የሚታዩ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና በንፁሃን ላይ የሚፈፅሙትን አሰቃቂ ግድያዎች በፍጥነት ሊያስቆም እንደሚገባም ያነሳሉ።

ከእነዚህ ታጣቂዎች እና ከጥቂት የፖለቲካ ነጋዴዎች በስተጀርባ እነማን አሉ የሚለውን መመርመር ይገባዋል ባይ ናቸው። ሰላም እና ፀጥታን በማስጠበቅ የሀገር ውስጥ ፖለቲካው እንዲሰክን በማድረግ፣ ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ዘብ መቆም የሚያስችል ሁነት መፈጠር ይገባዋልም ነው የሚሉት አቶ ውብእግዜር ፈረደ፤ የውስጥ ጥንካሬ ለውጭው ተጋላጭነት መመከቻ ዋናው ጋሻ ነው በሚል።

የትራምፕን የሚያበሳጭ እና የሚያናድድ ንግግር ወደ በጎ መድረክ መቀየርም ይገባል የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ።
እነዚህ አስተያየት ሰጭዎች በቅርቡ ግድቡን ለማጠናቀቅ 40 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ መነገሩን እንደ መነሻ ወስደው አሁናዊውን የህዝብ ስሜት በመጠቀም የገንዘብ ማሰባሰቡን ሂደት ማጠናከር ይገባልም ይላሉ፤ ትልቁ የዲፕሎማሲ ስኬት የግድቡ መጠናቀቅ እና ውሃ መያዝ መሆኑን በመጠቆም።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለው በታላቁ ወንዝ ዓባይ ላይ ነው። ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ከአሁን በፊት እንደተናገሩት ታላላቅ ወንዞች ደግሞ የየሀገሩ ማንነት መገለጫዎች የትውልድ ቅብብሎሽ ምልክቶች ናቸው። ዓባይም ለኢትዮጵያ እንዲያ ነው።

በስላባት ማናዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.