Fana: At a Speed of Life!

ቀጠናውን ወደነበረበት ለመመለስ የተቋቋመው የአጎራባች ክልሎች ግብረ ሃይል ያከናወናቸውን ስራዎች ገመገመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን እየተስተዋለ ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከፌደራል መንግስት እና አጎራባች በሆኑት ክልል የተውጣጣው የከፍተኛ አመራሮች ግብረ ሃይል በህብረተሰቡ በኩል በተነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ለማበጀት ያከናወናቸውን ስራዎች ገምግሟል።

በውይይቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል ወርቅነህ ጉደታን ጨምሮ የአማራ፣ የኦሮሚያ እንዲሁም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ተገኝተዋል።

በዞኑ ውስጥ በህብረተሰቡ በኩል የሚነሱ የመሰረተ ልማት አለመሟላት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀጠናውን ከታጠቁ ሃይሎች ነጻ ለማድረግ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደፈጠረበት የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮለኔል ወርቅነህ ጉደታ አውስተዋል።

በቀጠናው ሰላምን ለማስፈን ከፌደራልና ከሶስቱ ክልሎች ከተውጣጡ ቡድኖች በኩል የተነሳውን የመፍትሄ ሃሳብ መውሰድ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ለውጡን በተፈለገው ፍጥነት ወደ ህዝቡ በማውረድ እና ለማስተማር የሚደረገው የአመራር ምደባ ጉዳይ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባውም ግብረ ሃይሉ ገልጿል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው በየደረጃው የሚነሱ ሁሉን ዓቀፍ ጥያቄዎችን በአጭር እና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን በመለየት እና ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በኩል ህዝቡን ብዥታ ውስጥ የሚከትና አመኔታን የሚያሳጣ መግለጫዎ ከመስጠት መቆጠብ እንዳለባቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በየደረጃ ባለው የጸጥታ መዋቅር አማካኝነት አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላም እየተመለሰ መሆኑን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.