Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችለውን ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችለውን ውይይት ከፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን ጋር አካሂዷል።

ምክር ቤቱ ከፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የፌዴራል ድጎማ እና የማከፋፈያ ቀመሮች ለማዘጋጀት የሚረዳ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ስራ ማስጀመሪያ ውይይት ነው ያካሄደው።

የመረጃ አያያዝ ስርዓቱ ለቀመር ዝግጅት የሚረዱ መረጃዎችን በማደራጀትና በመተንተን በሚፈለገው መልኩ ለውሳኔ አስፈላጊ የሆኑ ሪፖርቶችን ያወጣልም ነው የተባለው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ 7 የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎችን በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር የመወሰን ሥልጣን ተሰጥቶታል።

የገቢ ክፍፍል ቀመር ዝግጅት ደግሞ ሰፊ መረጃዎችን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ፍትሃዊና ውጤታማ የፌዴራል ድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ጥራት ያላቸው የፊስካል፣ የስነ ሕዝብ እንዲሁም የማኅበረ ኢኮኖሚ መረጃዎች መኖርና በአግባቡ አደረጃቶ መያዝን ይጠይቃል ነው የተባለው።

ስለሆነም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ሥርዓት በገቢ ክፍፍሉ ሂደትና ውጤት ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም የፌዴራል መንግሥቱ እና ክልሎች ግልጸኝነትና መተማመን እንዲኖራቸው እንደሚረዳ በባለሙያዎች ማብራሪያ መሰጠቱም ተገልጿል።

የመረጃ ስርዓቱ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ፍላጎትና ከምክር ቤቱ ልዩ ባህሪይ ጋር የሚጣጣም ፣ ከአሁን በፊት የነበረውን የመረጃ ክፍተት የሚያሟላ ፣ ለአጠቃቀም ቀላል እንዲሆንና ደህንነቱም ለአደጋ የማይጋለጥ መሆን እንዳለበት አፈ ጉባዔው አሳስበዋል።

ከዚያም ባለፈ የዝርጋታ ስራውን ልምድ ካለው ከፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጻዋል።

የመረጃ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚዘረጋው ኤክሲድ የተባለ አማካሪ ድርጅት መሆኑንም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.