Fana: At a Speed of Life!

የከተማ አስተዳደሩ ከብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ድርጅት ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ከተባለ የአለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት ግብረሰናይ ድርጀት ጋር የ15 ሚሊን የአሜሪካ ዶላር (555 ሚሊየን ብር) የትብብር ስምምነት ተፈራረመ።

በዛሬው እለት የተፈረመው የትብብር ስምምንቱ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ መሆኑንም የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በስምምነቱ ወቅት፥ አዲስ አበባ ከ30 አለም አቀፍ ከተሞች አንዷ ሆና የብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ሶስተኛ ምዕራፍ የመንገድ ደህንነት ስራዎች ላይ እገዛ በማግኘቷ በከተማዋ ለሚተገበሩ እና ተጨባጭ ለውጥ ለሚያስገኙ የመንገድ ደህንነት ማሻሻያ ስራዎች ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

ድጋፉም ዜጎች ከህይወት ክፍያ ነፃ እንቅስቃሴ ለማረጋግጥ ወደ ሚደረገው ግብ ያደርሰናል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፥ የከተማ አስተዳደሩም የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የብሉምበርግ ፍላንትሮፒስ ኬሊ ላርሰን በበኩላቸው፥ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት እና የአካል ጉዳት ለመቀነስ ቁርጠኛ በሆነው ኔትዎርክ እና የብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ፕሮጀክት ላይ ከሚሳተፉ 30 ከተሞች አንዷ በሆነችው ከአዲስ አበባ ጋር በጋራ ለመስራት መቀጠላቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በትራፊክ አደጋ የሰዎችን ህይወት ለማዳን እርምጃዎችን እየወሰዱ ለሚገኙት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤም አድናቆታቸውን አቅርበዋል።

ለዘንድሮ የስራ ማስኬጃ እና ለቴክኒካል ድጋፍ 15 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል።

ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ከተማ እንደ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እና ጠጥቶ ማሽከርከር ዋና የመንገድ ትራፊክ የአደጋ መንስኤዎች ላይ በማተኮር የከተማ አስተዳደሩን ሲደግፍ ቆይቷል።

ፕሮጀክቱ የተሻሉ ዓለም አቀፍ አሰራሮችን ለመተግበር ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በማጣመር እና የመንግስት ኤጀንሲዎች እና በከተማዋ ውስጥ በመንገድ ደህንነት ላይ የሚሰሩ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂዎችን ተቋማዊ የማድረግ ስራዎች ላይ እገዛ አድርጓል።

የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ደህንነትን ለማሻሻል የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በመንደፍ በአለፉት ሶስት የትግበራ ዓመታት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል።

የብሉምበርግ ኢንሽዬቲቭም በትግበራ እቅዱ ላይ የተካተቱ ተግባራት ላይ እገዛ እያደረገ ነበረ ሲሆን፥ የእቅዱ አካል የሆነውን የጠጥቶ ማሽከርከር የአደጋ መንስኤ ላይ የተገኘዉን ከ10 በመቶ ወደ 2 ነጥብ 5 በመቶ  የመቀነስ ውጤት ላይ ለምሳሌ ላቅ ያለ ሚና ነበረው፡፡

ይህን ውጤት ለማስቀጠልም አስተዳደሩ አዲስ የ3 አመት የመንገድ ደህንነት መተግበሪያ እቅድ አዘጋጅቶ የመንገድ ደህንነት ካውንስሉ አባል ከሆኑ ባለድርሻ አካላት እና እንደ ብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ያሉ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደሚሰራም አስታውቋል።

ድጋፉ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው 15 ሀገሮች እና 30 ከተሞች የ600 ሺህ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ እና እስከ 22 ሚሊዮን የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል ያለመ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.