Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚካሄደው የህዳሴ ግድብ ውይይት ውጤት አመርቂ ይሆናል – ሙሳ ፋቂ ማህማት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በሚካሄደው የህዳሴ ግድብ ውይይት ላይ ደስተኛ መሆናቸውን ገለፁ፡፡

ሊቀ መንበሩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚካሄደው የህዳሴ ግድብ ውይይት አመርቂ እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል፡፡

ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ያሻል በሚል ፅንሰ ሀሳብ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲታይ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሊቀመንበሩም የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች ውይይት በጠንካራ የአፍሪካ ህብረት አመራር ሰጭነት ስር ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ትናንት ባካሄዱት ውይይት በሰባት ቀናት ውስጥ ድርድሩን በማካሄድ በቀጣይ የድርድሩ አካሄዶች እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ስምምነት መድረስ፣ ልዩነት ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ልዩነትን ለማጥበብ እና ውጤቱንም ለውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቀጣይ ስብሰባ ለማቅረብ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት በበይነ-መረብ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በመድረኩም የመጀመሪያው የቴክኒክ ስብሰባ በሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትር ሰብሳቢነት ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡

በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የሚደረገው ውይይት ሃገራቱ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው፡፡

ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር እንደምትሰራ ከዚህ ቀደም ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታም የተፋሰሱ ሃገራት የውሃ ተጠቃሚነትና ድርሻ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማያሳርፍ መልኩ እንደሚካሄድም መግለጿ ይታወሳል፡፡

ባሳለፍነው ወር መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድርድሩ ይቀጥላል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት ስድስት ሳምንታት ተቋርጦ መቆየቱ አይዘነጋም።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከሶስቱ ሃገራት መሪዎች ጋር ተወያይተው ድርድሩ እንደገና እንዲቀጥል በተስማሙት መሰረት ነው የሶስትዮሽ ድርድሩ ካቆመበት የቀጠለው፡፡

በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ በሚደረገው የሶስትዮሽ ውይይት ሰላማዊ እና ትብብራዊ መፍትሄ ለመስጠት በሶስቱ ሀገራት መሪዎች ዘንድ ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና ተነሻሽነት እንዳለው ተነስቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.