Fana: At a Speed of Life!

የጤና ሚኒስቴር የጡት ካንሰር ህክምና በ12 ሆስፒታሎች እየተሰጠ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 12 ሆስፒታሎች የጡት ካንሰር ህክምና እየሰጡ እንደሚገኙ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የጡት ካንሰርን ወር በማስመልከት የጤና ሚኒስቴር ጡትዎን በእጅ በመዳሰስ እና በመመርመር የጡት ካንሰርን ይከላከሉ በሚል መሪ ቃል ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሯ 65 በመቶ የሚሆኑት የበሽታው ታማሚዎች ወደ ህክምና ተቋም ዘግይተው መሄዳቸው ትልቅ ተግዳሮት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በቂ የሆነ የጡት ካንሰር የህክምና ማዕከላት አለመኖርም የጤና ስርዓቱ ላይ ሌላኛው ችግር እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

የጤና ሚኒስቴር የጡት ካንሰር ህክምና ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን 12 የክልል ሆስፒታሎች ላይ ሃኪሞችን በማሰልጠን አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡

ይህም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላይ ያለውን ጫና በከፍተኛ መልኩ ከመቀነሱም በላይ ለኬሞ ህክምና የሚያስፈልገውን ስድስት ወር የመጠበቂያ ጊዜ ከሁለት ሳምንት በታች አድርጎታል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የስድስት ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ወራት ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቅድስት ብርሃኑ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.