ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በሚመለሱበት ወቅት ለችግር እንዳይጋለጡ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በሚመለሱበት ወቅት ለትራንስፖርት እና ለሌሎች ችግሮች እንዳይጋለጡ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማስቀጠል ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በዚህ መሰረትም የ2012 ዓ.ም ቅድመ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎች ከፊታችን ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው በመመለስ የገፅ ለገፅ ትምህርት የሚጀምሩ ይሆናል፡፡
በዚህ ወቅትም ተማሪዎች ለትራንስፖርት እና ለሌሎች ተያያዥ ችግሮች እንዳይጋለጡ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ነው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ያስታወቀው፡፡
በባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኛ፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመለሱ ተመራቂ ተማሪዎች አስተማማኝ የትራንስፖርት አቅርቦት መኖሩን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግም ለሁሉም መናኸሪያዎች አቅጣጫ መቀመጡን ነው የገለጹት፡፡
በዚህ መሰረትም በመነኻሪያዎች ተጓዦች አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን እንዲጠቀሙ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በመነኻሪያዎች የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በቫይረሱ የሚጠረጠሩ ተጓዦች ከተገኙም ለይቶ ማቆያ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎችም በጉዟቸው ወቅት በጤና ሚኒስቴር የተቀመጡትን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች ገቢራዊ በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ