Fana: At a Speed of Life!

1ሺህ 495ኛው የነብዩ መሐመድ መውሊድ በዓል ውስን አማኞች በተገኙበት በታላቁ አንዋር መስጊድ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት 1ሺህ 495ኛው የነብዩ መሐመድ የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ ውስን ዓማኞች በተገኙበት እንደሚከበር ገለጸ፡፡
 
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጁ ዑመር በመልዕክታቸው ምዕመኑ የመውሊድ በዓልን የሚያከብረው የነቢዩ መሐመድን አስተምህሮ በመተግበርና ተምሳሌታዊነቱን ለማስቀጠል ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
 
እንዲሁም የመውሊድ በዓልን ቀኑን ለማክበር ሳይሆን በዛን ጊዜ ለሰው ልጆች ፈጣሪ የዋለውን ውለታ ለማወደስና ለማመስገን ነው ብለዋል።
 
በተጨማሪም በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አሊ መሃመድ ሺፋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
በዚህ ወቅት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ነዋሪዎች የማዕድ ማጋራት ስነ ስርዓት ተካሄዷል፡፡
 
ምክር ቤቱ በዓሉን በተለያዩ ደማቅ ስነስርዓቶች ለማክበር ቢያስብም በሃገሪቱ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ5 ሺህ ያልበለጠ ሰው በሚታደምበት ለማክበር መገደዱንም ነው የተናገሩት፡፡
 
አያይዘውም አሁን በሀገሪቱ እየገጠሙ ያሉ ተፈጥሯዊ ችግሮች መልካቸውን እየቀያየሩ ፈተና እንዳይበዛ እና አሁን ያለውን አንበጣና ሌሎችንም ችግሮቸ ለመቋቋም ዱዓ ማድረግና ሶደቃ ማብዛት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
 
በመልዕክታቸው ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ የሀገሩን ሰላምና አንድነት እንምዲሁም ልማትን ማስቀጠል ላይ ያለምንም ልዩነት ሊረባረብና ሊሰራ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
 
 
በሙሀመድ አሊ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.