የክልልና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች ኮቪድ-19ኝን ያማከለ የጤና አገልግሎት በመስጠት አመርቂ ስራዎች ሰርተዋል- ዶ/ር ሊያ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የክልሎች እና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች የኮቪድ-19 ወርርሽኝን ያማከለ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት በመስጠት አመርቂ ስራዎች ማከናወናቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ሕጻናትና ስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ሲካሄድ የነበረው የ2012 ዓ.ም አመታዊ የስራ አፈጻጸም ግምገማ መካሄዱን የሚኒስቴሩ መረጀ ያመለክታል።
በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ካለፈው አመት የተገኙ ተሞክሮዎችን በመጠቀም በቀጣይ በእናቶችና ህጻናት ጤና ረገድ ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራት ላይ አመራር ሰጥተዋል።
ዶክተር ሊያ ከክልሎች እና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች በቀረበው ሪፖርት መሰረት የኮቪድ-19 ወርርሽኝን ያማከለ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት በመስጠት አመርቂ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በቀጣይም መልካም አፈጻጸሞሞችን በማስቀጠል፣ የታዩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ለተሻለ ውጤት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አያይዘውም መሰረታዊ የህክምና አገልግሎቶችን በተቀናጀ መንገድ መስጠት እንዲቻል አቅጣጫ ሰተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፥ የእናቶችና ሕጻናት ጤና ከፍተኛውን የጤና ሽፋን የሚይዝ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በዘርፉ ለሚሰጠው ሁሉን አቀፍና የተሟላ አገልግሎት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አንስተዋል።
በቀጣይም መደበኛ የሆኑ የጤና አገልግሎቶችን በአግባቡ መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።