Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ የተሰረቀውና ኢየሱስ ክርስቶስ የእሾህ አክሊል የደፋበት ስዕልን ጨምሮ ዓለም ላይ 10 ወሳኝ ቅርሶች እየተፈለጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ እና በብሪታኒያ መካከል በመቅደላ በተካሄደው ጦርነት ወቅት የተሰረቀውና ኢየሱስ ክርስቶስ የእሾህ አክሊል የደፋበት ስዕልን ጨምሮ 10 ቅርሶችን የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ ነው።
የጥንታዊ ቅርሶች አፈላላጊ የሆነው ቡድን ከተለያዩ ሀገራት ተሰርቀው የት እንዳሉ ያልታወቁ ተፈላጊ 10 ጥንታዊ ቅርሶችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
ከዚህ ውስጥም በኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ መካከል በመቅደላ በተካሄደው ጦርነት የተሰረቀውና የእሾህ አክሊል የተደፋበት የኢየሱስ ክርስቶስ ስዕል አንዱ ነው።
ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ቀደም ባለው ጊዜ በኢትዮጵያውያን እንደተሳለ የሚገመተው ይህ ስዕል ኢየሱስ ክርስቶስ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ወደ መሬት ሲመለከት ያሳያል፡፡
ይህ ስዕል በወቅቱ በነበረው ጦርነት ከአጼ ቴዎድሮስ ምሽግ በብሪታኒያ ወታደሮች ከተዘረፉት ቅርሶች መካከል አንዱ ሲሆን የት እንደሚገኝ ግን አይታወቅም።
ከኢትዮጵያ ተሰርቆ ከሄደው ቅርስ በተጨማሪ በሜሶፖታሚያ ዘመን ከዝሆን ጥርስ የተሰራ ቅርፃ ቅርፅ ከኢራቅ፣ ከካምቦዲያ የተሰረቀ የጋኔሽ ሀውልት፣
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከቻይና ወደ አሜሪካ ሲጓጓዝ የነበረ የሆሞ ኢሬክተስ ቅሪተ አካል እና በአረንጓዴ ድንጋይ ላይ የተቀረፀ የፀሀይ አምላክ ምስል ከጓቲማላ ይገኙበታል።
እንዲሁም ከህንድ እና ከየመን የተሰረቁ ሌሎች ቅርሶች በአፈላላጊ ቡድኑ ዓለም ላይ ከሚፈለጉ 10 ውድ ቅርሶች መካተታቸውን ዘ አርት ኒውስ ፔፐር ያወጣው ዘገባ ያስረዳል፡፡
የቡድኑ ሊቀመንበር ዲቦራ ሌኸር አሁንም የት እንዳሉ ያልታወቁ በርካታ ድንቅ ስራዎች እንዳሉ ማስታወስ እፈልጋለሁ ብለዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.