Fana: At a Speed of Life!

ራክሲኦ ግሩፕ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የግል የመረጃ ቋት ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ራክሲኦ ግሩፕ ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠውን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የግል የመረጃ ቋት ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ።

የመረጃ ማዕከሉን ለመገንባት የሚያስችለውን ቦታ በአዲስ አበባ የአይሲቲ ፓርክ ያገኘ ሲሆን በፈረንጆቹ 2021 ሶስተኛው ሩብ ዓመት ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ በተሟላ፣ ዘመኑ በደረሰበት እና ቀዳሚ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች በምቹ አካባቢ ለደንበኞች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ከሚገኘው ለውጥ ጋር ተያይዞ ለቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፍቃድ ለመስጠት ዝግጅት ላይ በመሆኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በፍጥነት እንደሚያድግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰንደኮ ደበበ ተናግረዋል።

ግሩፑ በኢትዮጵያ መሰማራቱ የዲጂታል መሰረት ልማት አቅምን ለማሳደግ እና ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የገለፁት።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በሀገሪቱ የአይሲቲ ሴክተር እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከሚኖረው የራክሲኦ ግሩፕ መረጃ ማዕከል ግንባታ ጋር በትብብር መስራታችን ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የአይሲቲ አቅሙ ለመጪዎቹ አምስት አመታት 1 ነጥብ 5 ሜጋዋት እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን የፍላጎት መጠኑ ታይቶ ወደ 3 ሜጋ ዋት ከፍ ሊል እንደሚችል ካፒታል ሚዲያ ዘግቧል።

የራክሲኦ መሰረተ ልማት የሞባይል ኔትወርክ ኦፕሬተሮች፣ የይዘት ማቅረቢያ ኔትወርኮች እና የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወሳኝ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓታቸውን እንዲመሩ እንደሚያስችል የተቋሙ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙሊን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.