የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዳሴ ግድብን ከደለል ለመታደግና የዓባይ ተፋሰስን በቆላ ቀርከሀ ለማልማት ስምምነት ተፈረመ

By Tibebu Kebede

October 30, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለል ለመታደግ የዓባይ ተፋሰስን በቆላ ቀርከሀ ማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲቲዩት፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተፈራርመውታል፡፡

በመጀመሪያው ዙር በቆላ ቀርከሀ ለማልማት የታሰበው የደጀን እና የጎሀጽዮን የዓባይ ተፋሰስ ቆላማ አካባቢዎችን ነው ተብሏል፡፡

የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲቲዩትም የቆላ ቀርከሀ ዛፍ ችግኞችን እያባዛ መሆኑን ገልጿል፡፡

እስካሁን ድረስ 10 ሺህ ችግኞችን ማባዛቱን የጠቀሰው ኢንስቲቲዩቱ በቀጣይም 500 ሺህ ለማባዛት ማቀዱን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

የቆላ ቀርከሀ የዓባይ ተፋሰስ በደለል እንዳይሞላ እና ሥነ ምኅዳሩ እንዲያገግም ከማድረግ ባለፈ ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡