Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ተመሰረተ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም “የተሻለ ከተማ ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ቃል የከተሞች ፎረም የመመስረቻ ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ ተካሄዷል፡፡

ፎረሙ የከተማ ከንቲባዎች ተገናኝተው በወቅታዊ የከተሞች የትኩረት አጀንዳ ላይ ጽሁፍ ቀርቦ የሚወያዩበት፣ የተሻለ አሰራር ካላቸው ከንቲባዎች ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ያጋጠማቸው ፈተና ካለም መፍትሔ በጋራ የሚያፈላልጉበት እና የተሻለ አፈጻጸም ላከናወኑ ከንቲባዎች ዕውቅና የሚሰጥበት ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ሀገር በቀል የሆነ እውቀት እንዲጎለብት ማበረታታትና ከተሞች ከከተሞች ጋር የሚኖራቸውን ትብብርና ትስስር ማመቻቸት የፎረሙ አንዱ አላማ መሆኑን ከከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እንዲሁም ተግባር ተኮር የሆኑ ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን ማስፋፋት እና ሌሎችም እንዲጠቀሙበት ማስቻልን ዓላማው አድርጓል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ፎረሙ የከተማ ከንቲባዎች እና አመራሮች የነዋሪዎቻቸውን ችግሮች ለመፍታት በጋራ እንዲመክሩ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የከተማ ከንቲባዎች በበኩላቸው ፎረሙ በከተሞች ለሚታዩ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማምጣትና የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.