የሀገር ውስጥ ዜና

በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ሙዝዬም ሊገነባ ነው

By Tibebu Kebede

October 31, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተመሠረተው ዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ሙዚየም ሊገነባ ነው፡፡

በጣና ማዕከላዊ ሥፍራ ላይ ከደቅ ደሴት አጠገብ የሚገኘው ይህ ገዳም በርካታ ሐይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘ ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡

ከተገነባ ከ300 ዓመታት በላይ የሆነው የገዳሙ ሙዚየም ያለውን ቅርስ በተደራጀ መልኩ ለማስቀመጥ ምቹ ባለመሆኑ ሐብቶቹ ለአደጋ መጋለጣቸው ይነገራል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታትም አዲስ ሙዚየም ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ እና የባህር ዳር ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሐምን ጨምሮ የክልልና የፌደራል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሐይማኖት መሪዎችና ሌሎች የሐይማኖቱ ተከታዮች በተገኙበት ነው የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው።

ሙዚየሙ የረጅም ዓመታት ሐይማኖታዊ ቅርሶችን በተደራጀ መልኩ ለመሰነድና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ያግዛል መባሉን አብመድ ዘግቧል።