Fana: At a Speed of Life!

ዝርፊያ የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት የሰጣቸውን መሳሪያ ተጠቅመው ዝርፊያ የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በእስራት መቀጣታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የክሱ ዝርዝር እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ወንድሙ ሞሲሳ እና 2ኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ደረሰ ማርቆስ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ዲ ኤች ገዳ የገበያ ማዕከል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዝርፊያ ፈጽመዋል።

ተከሳሾቹ ካልተያዙት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ወንጀል ለመስራት አቅደውና ተስማምተው ለወንጀሉ መፈፀሚያ የሚሆን ክላሽ የጦር መሳሪያ እና ዱላ እንዲሁም መኪና በመያዝ ወንጀሉን ፈጽመዋል ተብሏል።

የፖሊስ አባላቱ የግል ተበዳይ አሚር አሊ እና በወቅቱ ሱቅ ውስጥ የነበረውን ዳውድ አሊን በያዙት ካቴና በማሰር እና በመደብደብ ካልተያዘው ግብረ አበራቸው ተክለሃይማኖት ገብረመድን ጋር በመሆን ወንጀሉን መፈጸማቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ ወቅት ሱቅ ውስጥ የተቀመጠውን 200 ሺህ ብር በመያዝና ባዘጋጁት መኪና የግል ተበዳዮቹ ከሱቃቸው አርቀው ጨለማ ቦታ በመውሰድ ተሰውረዋል ተብሏል።

በተደረገ ክትትልም 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ ተይዘው ዐቃቤ ህግ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት ከባድ የዝርፊያ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾች ክሱ ተነቦላቸው እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ የወንጅል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የምስክር ቃል ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የወንጀል ችሎት ተከሳሾችን ጥፋተኛ በማለት ወንጀሉን የፈፀሙት የፖሊስ አባል ሆነው በመሆኑ ማክበጃ በመያዝ፥ 1ኛ ተከሳሽ በ11 አመት እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ በ10 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ከጠቅላይ ‘ቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.