የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የበቆሎ መጋዝን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ሊጀምሩ ነው
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የበቆሎ መጋዝን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ሊጀምሩ መሆኑን አታወቁ።
አገልግሎቱ አምራቾች ወይም ተገበያዮች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዝን ምርታቸውን በማስገባት ለምርታቸው የተሰጣቸውን የዋጋ ደረሰኝ ብቻ እንደማስያዣ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአጭር ጊዜ የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ አገልገሎቱ ለግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ ተደራሽነትን ይበልጥ እንደሚያሳድግ ጠቅሰው፥ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶችም አዲስ እድል መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ አቦዬ በበኩላቸው፥ የብድር አገልገሎቱ በርካቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለሀገር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ አገልገሎቱን ለመጀመር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኘሁ በብድር አገልግሎቱ የተቋማቱ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ተቋማቱ አሁን በበቆሎ ምርት የጀመሩትን የመጋዝን ደረሰኝ አገልገሎት ወደፊትም በሌሎች ምርቶች እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ ከዓለም ባንክ አለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ምርት ገበያው በቡሬና ነቀምት ከተሞች ባሉት መጋዝኖች አማካኝነት እንደሚጀመር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።