Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋው ኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምዕራብ ወለጋ ሰላማዊ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥ መንግስት የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ በማገናዘብ የልማት ስራዎችን፣ የሰላም እና የስርዓት ግንባታ ላይ እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ከለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ሀይሎች በህዝቡ ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ መሆኑን አስታውቋል።
የጥፋት ሀይሎቹ መንግስት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ባለበት ወቅት በተቃራኒው በመቆም ጭቃኔ የተሞላበት ተግባር በህዝቡ ላይ እየፈፀሙ ነው ብሏል።
የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ከህውሃት ጋር በመሻረክ በኦሮሚያ ክልል እና በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ በተለያዩ ወቅቶች የግጭት አጀንዳዎችን በማዘጋጀት በሚዲያ በማሰራጨት እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ በገቡ የጦር መሳሪያዎች በፀጥታ ሀይሎች፣ በመንግስት መዋቅር እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የግድያ እርምጃ በመውሰድ ችግሮችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብሏል መግለጫው።
ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በተፈፀሙ በእነዚህ ተግባራትም በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እንዲፈጠር፣ በስጋት እንዲሞላ እና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ራሱን ቆጥቡ በረሃብ እና በጥማት እንዲጎዳ እያደረጉ ነውም ብሏል።
በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አቅጣጫ በሚገኙ ዞኖች ህፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ወጣቶችን ጨምሮ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲገደሉ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው እንዲሁም የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉ ይታወቃልም ብሏል፡፡
ከሁሉም በላይ በጫካ ውስጥ መሽጎ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወረው ኦነግ ሸኔ ሰዎችን ጠልፎ በመውሰድ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱ ያወሳው መግለጫው፤ በተለያዩ ጊዜያትም የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላት በተመሳሳይ መንገድ ጫካ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ሲያደርግ ቆይቷልም ነው ያለው።
የኦነግ ሸኔ ሽፍታ እስካሁን በፈፀማቸው የሽብር ተግባራት በርካታ ቤተሰቦች ተበትነዋል፣ ህፃናትን ያለ አባትና እናት አስቀርቷል ያለው መግለጫው፥ የህዝቡና የግለሰቦች ሀብትም እንዲጠፋ ማድረጉን አስታውሷል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ያለውን ተልዕኮ እና ሀላፊነት ለመወጣት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በስፋት እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
የህወሓት ተላላኪ የሆነው ይህ የኦነግ ሸኔ ቡድን ህዝቡ እና መንግስት በጋራ በመሆን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱት ባለው እርምጃ ለመጥፋት መቃረቡንም መግለጫው አመላክቷል።
እየተወሰደ ባለው እርምጃ የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ይህ ቡድን ተስፋ በመቁረጡ በአንድ ስፍራ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጥቃት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል።
በትናትናው እለትም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቀናቲ ቀበሌ ጨለማን ተገን በማድረግ በፈፀመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉንም ነው የገለጸው።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከህዝቡ እንዲሁም የፀጥታ እና አስተዳደር አካላት ጋር በመሆን እነዚህ ሽፍታዎች የገቡበት ቦታ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።
በተፈፀመው ጥቃት ለተሰው ወገኖች የተሰማውን ሀዘን የገለፀው የክልሉ መንግስት ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.